የኤለን መስክ ኩባንያ በብራዚል ህጋዊ ወኪሉን እንዲመርጥ በፍርድ ቤት የተቀመጠለት ገደብ ተጠናቋል
መስክ እና የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ ሰጣ ገባ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል
ብራዚል የኤለን መስክ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) በሀገሪቱ ውስጥ እንዳይሰራ ማድረግ ጀመረች።
የሀገሪቱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁጥጥር ተቋም አናቴል የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ደንበኞቻቸው ከዛሬ ጀምሮ ኤክስን እንዳይጠቀሙ እንዲያደርጉ ማሳሰቡን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በዚህም በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል የማህበራዊ ትስስር ገጹን በኮምፒውተርም ሆነ በሞባይል ላይ መጠቀም አስቸጋሪ ሆኗል ነው የተባለው።
ብራዚል ይህን እርምጃ የወሰደችው የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድቤት ዳኛ አሌክሳንደር ደ ሞራይስ በትናንትናው እለት ያሳለፉትን ውሳኔ ተከትሎ ነው።
ዳኛ ሞራይስ ኤክስ የብራዚል ተወካዩን በ24 ስአት ውስጥ እንዲመርጥ ባለፈው ረቡዕ የጊዜ ገደብ ቢያስቀምጡም ኩባንያው ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱ አስቆጥቷቸዋል።
“ኤለን መስክ ለብራዚል ሉአላዊነት በተለይም ለፍትህ ስርአቷ ምንም አይነት ክብር እንደሌለው ኣአሳይቷል፤ ራሱን የተለየ ዜጋ አድርጎ ከሁሉም ሀገር ህግ በላይ ለመሆን ይሞክራል” ሲሉም ዳኛው በትናንትናው እለት ኤክስ በብራዚል እንዲዘጋ ወስነዋል።
የማህበራዊ ትስስር ገጹ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እስካላከበረ ድረስ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይና ቪፒኤን ተጠቅመው መተግበሪያውን በሚጠቀሙ ሰዎችና ኩባንያዎች ላይም 8 ሺህ 900 ዶላር ቅጣት እንደሚጣል ማሳወቃቸው ተዘግቧል።
ከብራዚል 20 በመቶው (40 ሚሊየን) የሚጠጉ የኤክስ ተጠቃሚዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኩባንያው ስራ አስፈጻሚ ሊንዳ ያካሪኖ የዛሬው የእገዳ ዜና “በመላው አለም ለሚገኙ በተለይም ለብራዚላውያን የኤክስ ተጠቃሚዎች ልብ ሰባሪ ነው” ብለውታል።
የብራዚል ከፍተኛ ፍርድቤት ዳኛ አሌክሳንደር ደ ሞራይስ እና ቢሊየነሩ ኤለን መስክ ሰጣ ገባ ውስጥ የገቡት ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ነበር።
ፍርድቤቱ የተዛባ መረጃ የሚያስራጩ ናቸው ያላቸውን ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች አካውንት እንዲዘጋ ለመስክ ያቀረቡት ጥያቄ በጎ ምላሽ አላገኘም።
ቢሊየነሩ የዳኛውን ውሳኔ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለውና የመናገር መብትን የሚጣረስ በሚል ማጣጣሉም አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎም የኤክስ የባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውንና የኩባንያው የብራዚል ተወካይ ለእስር እንደሚዳረግ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ይደርሰው እንደነበር ኤክስ አስታውቆ ነበር።
AL AIN
More Stories
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፑቲን ጋር የሚያደርጉት ንግግር እየተመቻቸ መሆኑን ገለጹ።
የአሜሪካ ኮንግረስ በአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ድምጽ ሰጠ
አስደንጋጩ የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት አልበረደም