በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሁለት ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ስጋት ያለባቸው ነዋሪዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ወደ ሌላ ቦታ የማስፈር ስራ መጀመሩን የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በዞኑ በአንዳንድ ወረዳዎች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የመሬት መንሸራተት አደጋ በመከሰቱ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወ/ሮ ፍጹም ጌታሁን፤ ሰሞኑን በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ጎማ እና ጌራ ወረዳዎች የተለያዩ ቀበሌዎች ላይ የመሬት መንሸራተት አደጋ መከሰቱን ተናግረዋል።
አደጋው ሰፍቶ የሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ መከላከል ስራ መጀመሩን ገልጸው፤ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ የማስፈር ስራ መጀመሩን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚሁ መሰረት በጌራ ወረዳ 591 ነዋሪዎችን እንዲሁም ከጎማ ወረዳ 330 ነዋሪዎችን ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ የማስፍር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከነዚህ ወረዳዎች በተጨማሪ በሰቃ ጨቆርሳ፣ በሸቤ ሶምቦ፣ በሰጠማና በነዲ ጊቤ ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ የቅድመ መከላከል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የአደጋው ተጋላጮችን ከቦታው የማራቅ እና አደጋው የደረሰባቸውን ደግሞ መልሶ የማቋቋም እና የመደገፍ ስራ በቅንጅት እንደሚሰራ አክለዋል።
FBC
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።