ኢሰመጉ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተዳፍነው እንዲቀሩ የህግ ክፍተት አስተወጽኦ እንዳለው ባወጣው መግለጫ አስታውቋልየሴቶችና ህፃናትን አስገድዶ መድፈር እና ጥቃት የተመለከተው የወንጀል ህግ አስተማሪ በሆነ መልኩ እንዲሻሻል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) ጠየቀ፡፡ጉባኤው በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሴቶችና ህጻናት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች ከጊዜ ወደጊዜ የጨመረው ወንጀል ፈጻሚዎች አስተማሪና ተመጣጣኝ ቅጣት ባለመቀጣታቸውና ወንጀል ሰርቶ ያለመያዝ ልምድ በመበራከቱ ነው ብሏል፡፡የቅጣት አላማ በወንጀለኞች ላይ ተመጣጣኝ የሆኑ ውሳኔዎችን በመወሰን ጥፋተኛው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ህብረተሰቡን ማስተማር ይገባል ብሏል ጉባኤው፡፡በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣው የአስገድዶ መድፈር ተግባር ጾታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ያሉ ህጎች አላማቸውን እና ግባቸውን እያሳኩ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም ሲል ገልጿል። ኢሰመጉ በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ ነዋሪ ከሆነችው የህጻን ፌቨን የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ባለፈ ፤በክልሉ 92 ሴቶች ላይ አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑን አደረኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን ነው ያስታወቀው፡፡በተጨማሪም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደራሼ ዞን ሽላሌ ቀበሌ በቀን 16/11/2016ዓ.ም የ14 አመት ታዳጊ በ7 ሰዎች የተደፈረች መሆኑን እና ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየተዳፈኑ ነው ሲል ቅሬታውን ገልጿል፡፡የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከአንቀጽ 620 እስከ አንቀፅ 628 ያለው ክፍል ማንኛውም ሰው የኃይል ድርጊት በመጠቀም ወይም በብርቱ ዛቻ አንድን ሴት አስገድዶ ጥቃት የፈጸመ እንደሆነ በወንጀል እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ በዚህም የፌደራል መንግስት ከወንጀል ህጉ አላማና ግብ አንፃር የሴቶችና ህፃናትን አስገድዶ መድፈር እና ጥቃት የሚመለከተው ክፍል ላይ ተገቢውን ጥናት በማድረግ ህጉ ለሚፈጸሙት ወንጀሎች ተመጣጣኝና አስተማሪ በሆነ መልኩ እንዲሻሻል ጥረት እንዲያደረግ ኢሰመጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ኢሰመጉ በተጨማሪም የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የፍትህ አካላት በተለይም ፖሊሶች፥ ሴቶች እና ህጻናት ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አካላትን ትኩረት በመስጠትና ተገቢውን ክትትል በማድረግ ለፍትህ እንዲያቀርቡም ጠይቋል፡፡
Al-Ain
More Stories
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ከትራምፕ መመረጥ በኋላ የጎልፍ ጨዋታ ልምምድ ጀመሩ
ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ ሹመቶችን ለማን እንደሚሰጡ ፍንጭ ሰጡ
በ2025 ምርጫ የሚያደርጉ ሀገራት እነማን ናቸው?