October 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ዕዙ ያስመዘገባቸውን ድሎችና ያገኛቸውን ስኬቶች ከሕዝብ ጋር እያከበረ መሆኑን አስታወቀ

በኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ባለፉት 47 ዓመታት ያስመዘገባቸውን አንጸባራቂ ድሎችና በተሳተፈባቸው ታላላቅ የልማት ሥራዎች ያገኛቸውን ስኬቶች ከሕዝብ ጋር በጋራ እያከበረ መሆኑን አስታወቀ።ዕዙ የተመሰረተበትን 47ኛ ዓመት በዓል ማክበር ጀምሯል፡፡የምስረታ በዓሉን አስመልክተው የዕዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ በሰጡት መግለጫ÷ ዕዙ ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጥቃቶችን በመመከትና ድል በማስመዝገብ ያለፉትን 47 ዓመታት ታሪክ ሲያስመዘግብ መቆየቱን አስገንዝበዋል፡፡ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ አስደናቂ ታሪክ ሲያስመዘግብ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡ዕዙ ያስመዘገባቸው ድሎችን ከሕዝቡ ጋር በጋራ ለመዘከር 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡በአከባበሩ ላይም ዕዙ ያስመዘገባቸውን ድሎች በመያዝ ቀጣይ ግዳጅን በድል መወጣት የሚያስችል ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር የሕዝቡንና የሰራዊቱን አንድነት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሠራል ብለዋል፡፡ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዻጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሚከበረው በዓል ላይ÷ የትግል ሂደቱን በሚገባ የሚገልጽ ዶክመንተሪ፣ የተለያዩ ዝግጅቶች፣ ሰማዕታትን የሚዘክርና አሁን ያሉትን ጀግኖች በግልጽ አጉልቶ የሚያወጣ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ ይቀርባል ብለዋል፡፡ዕዙ በጦርነት ዐውድ ላይ የተጠቀማቸው የቡድን የጦር መሳሪያዎች እንደሚጎበኙ እና በጅግጅጋና ሐረር ከተሞች ያከናወናቸው የልማት ፕሮጀክቶችም እንደሚመረቁ አመላክተዋል፡፡

FBC