November 21, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢትዮጵያ በዋና ዋና መግቢያና መውጫዎች ላይ የዝንጀሮ ፈንጠጣ በሽታ ቁጥጥር ማድረግ ጀመረች

የአፍሪካ ሲዲሲ በ13 ሀገራት የተከሰተው በሽታ አሳሳቢ የህብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑን ገልጿልበሀገሪቱ ዋና ዋና መውጫ እና መግቢያ ቦታዎች ላይ የዝንጅሮ ፈንጣጣ በሽታ ቁጥጥር እያከናወነ እንደሚገኝ የጤና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡በኢትዮጵያ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና ሞያሌ እንዲሁም ሌሎች የመግቢያ ቦታዎች ላይ የቁጥጥርና ማጣራት ስራ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ነው ሚንስቴሩ የገለጸው፡፡በኢትዮጵያ እስካሁን በበሽታው የተያዘ ሰው አለመገኝቱ ይፋ ያደረገው ሚንስቴሩ በሽታው በቀጥታ ከሰው ወደ ሰው በንክኪ የሚተላለፍ እንደመሆኑ በመግቢያና መውጫ ኬላ አካባቢዎች ላይ የቁጥጥርና መከላከል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያለው ። የአፍሪካ ሲዲሲ ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ በ 13 የአፍሪካ ሀገራት፣ 2,863 ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዛቸው እና፤ 517 ለህልፈት መዳረጋቸዉ መረጋገጡን ጠቅሶ በሽታዉ የህብረተሰብ ጤና አህጉራዊ ደህንነት ስጋት መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ አክሎም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሁሉም የአፍሪካ ሃገራት የጋራ እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ህሙማን የሚያሳዩዋቸው ዋና ዋና ምልክቶች እንደ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት ናቸዉ። እነዚህ ምልክቶች መከሰታቸው የተረጋገጠ እና በቅርቡ በሽታው ወደ ተከሰተባቸው ሀገሮች የጉዞ ታሪክ ያለዉ ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊዉን ምርመራና እንክብካቤ ማግኘት እንዳለበት የጤና ሚንስቴር አሳስቧል።በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛዉም ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት ማድረግ ወይም በ952 እና 8335 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ገልጾ፤ ሁሉም አካላት ሊከተሏቸዉ የሚገቡ ሂደቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስመልክቶ በቅርቡ ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡በሽታዉ የህብረተሰብ ጤና አህጉራዊ ደህንነት ስጋት መሆኑን የገለጸው የአፍሪካ ሲዲሲ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እና ለመግታት ከአፍሪካ ህብረት 10.4 ሚሊየን ዶላር በጀት እንደተለቀቀለት አስታውቋል፡፡በመጪዎቹ ወራት 3 ሚሊየን ዶዝ ክትባት የሚያስፈልገው የአፍሪካ ሲዲሲ በቅርብ ጊዜ ማግኝት የሚችለው የክትማት መጠን ከ65 ሺህ ዶዝ እንደማይበልጥ ያስታወቀ ሲሆን፤ የክትባት እጥረት መኖር የበሽታው ስርጭት መጨመር ላይ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል፡፡የበሽታውን አለምአቀፋዊ ስጋትነት ለመወሰን የአለም ጤና ድርጅት በዛሬው እለት አስቸኳይ ጉባኤውን በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኬንያ ፣ ኮንጎ ፣ ብሩንዲ ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳን ጨምሮ በ13 ሀገራ እንደተከሰተ የተረጋገጠው በሽታው እስከ 15 ሺህ በሚጠጉ ሰዎች ላይ ሳይከሰት እንደማይቀር ተገምቷል፡፡በ2022 በተለያ ሀገራት በሰፊው ስርጭቱ እየጨመረ የነበረው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ባሳለፍነው አመት ግንቦት ወር ላይ ዓለም አቀፍ አጣዳፊ የጤና ስጋት መሆኑ ማብቃቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡በሽታው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በነበረበት ወቅት በ111 አገራት 87,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 140 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

AL-AIN

You may have missed