January 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

እስራኤል በተፈናቃዮች መጠለያ ጣብያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎች ተገደሉ

የተመድ መረጃ እንደሚያሳየው 99 በመቶ የጋዛ ነዋሪ ከቀየው ተፈናቅሎ በመጠለያ ጣብያዎች ውስጥ ይገኛል

እስራኤል በበኩሏ ስፍራው 20 የሀማስ ታጣቂዎች ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጁ የነበሩበት ነው ብላለች

እስራኤል በጋዛ ተፈናቃዮች ተጠልለው በሚገኙበት ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከ70 ባላይ ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

ጥቃት በተፈጸመበት ትምህርት ቤት በርካታ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ተነግሯል፡፡ 

ሟቾችን በተመለከተ ቢቢሲ እና ሮይተርስ 70 መሆናቸውን ሲዘግቡ አጃንስ ፍራንስ ፕረስ በበኩሉ ቁጥሩ ወደ 90 እንደሚጠጋ ዘግቧል፡፡ 

ጥቃት የተፈጸመበት አል ታባ ትምህርት ቤት እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ተጠልለው የሚገኙበት ሲሆን የአየር ጥቃቱ በቅጥሩ ውስጥ በሚገኝ መስጂድ የንጋት ጸሎት እያደረጉ በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ መፈጸሙ ተነግሯል፡፡

የእስራኤል መከላከያ ሀይል ቃል አቀባይ ጥቃቱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ትምህርት ቤቱ ሀማስ ለወታደራዊ ዘመቻዎች የሚጠቀምበት እና በስፍራውም 20 የሚደርሱ የቡድኑ ታጣቂዎች ይገኙ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ሌተናል ኮለኔል ናዳቭ ሾሻኒ እንደተናገሩት ተፈናቃዮችን ከለላ በማድረግ ከፍተኛ የሀማስ ወታደራዊ አመራር በስፍራው ዘመቻ ለመምራት ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር የተረጋገጠ መረጃ ደርሶናል ብለዋል፡፡

በጋዛ የጤና ባለስልጣናት የተነገረው የሟቾች ቁጥር የተጋነነ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ጥቃቱ ትክክለኛውን ኢላማ ታሳቢ አድርጎ የተፈጸመ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

እስራኤል በላፉት ሳምንታት በጋዛ ካን የኑስ እና በተለያዩ ስፍራዎች በሰፊው እያደረገችው ባለው ጥቃት የተለያዩ የተፈናቃይ መጠለያዎችን ኢለማ አድርጋ ጥቃት ፈጽማለች፡፡

እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ከሆነ በጋዛ ከሚገኙ 564 የትምህርት ቤት ህንጻዎች ውስጥ 477 በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጥቃት ሰለባ ሁነዋል፡፡

AL AIN