ኢራን በእስራዔል ላይ ጥቃት ለማድረስ መዛቷን ተከትሎ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሀገራቸው የደህንነት ቡድን ጋር መምከራቸው ተሰምቷል፡፡በኢራን የሐማስ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬ እና የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ ቁልፍ አዛዥ መገደላቸውን ተከትሎ በቀጣናው ውጥረት መንገሱ ይታወቃል፡፡በዚህም ኢራን፥ እስራዔል በሃኒዬ ግድያ ምክንያት ከባድ ቅጣት ይጠብቃታል ማለቷ ይታወሳል።ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ባይደን “ኢራን አጸፋዊ ምላሽ በእስራኤል ልታደርስ ትችላለች” የሚለው ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ከሀገሪቱ ከፍተኛ የብሔራዊ ደህንነት ቡድናቸው ጋር ተገናኝተው መክረዋል ተብሏል፡፡ባይደን፥ እስራኤል ጥቃት ቢደርስባት ለመደገፍ ስለሚደረገው ዝግጅት ገለጻ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው፥ ባለሥልጣናት እስራኤልን ከጥቃት ለመከላከል ሌት ተቀን እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል እንደቢቢሲ ዘገባ፡፡በምክክሩ የኢራን ጥቃት መቼ ሊፈጸም እንደሚችል እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ግልፅ አለመሆናቸው ለፕሬዚዳንቱ ተብራርቶላቸዋል።ይህም ቢሆን ግን ከአንድ ቀን በፊት ብሊንከን ለቡድን-7 አባል ሀገራት ኢራን እና ሂዝቦላህ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ውስጥ እስራኤልን ሊያጠቁ እንደሚችሉ መናገራቸው ተገልጾ ነበር።ባይደን ከገለጻው በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ በኢራን እና በአጋሮቿ የሚሰነዘሩ ዛቻዎች፣ ቀጣናዊ ውጥረቶችን ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችንና እስራኤል ጥቃት ቢደርስባት ለመደገፍ የተደረጉ ዝግጅቶችን በተመለከተ ወቅታዊ መረጃዎችን አግኝተናል ብለዋል።በአሜሪካ የጦር ኃይሎች ላይ ለሚሰነዘረው ጥቃት በመረጥነው መንገድ እና ቦታ ምላሽ ለመስጠት እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ሲሉም ነው ያከሉት፡፡ሁሉም ወገኖች ከመካረር መቆጠብ አለባቸው ፤ ለማንም አይጠቅምም ወደ ባሰ ግጭትና ሰላም ማጣት ብቻ ነው የሚሄደው ሲሉ ያስጠነቀቁት ብሊንከን፤ የተኩስ አቁም ስምምነት በጋዛ ብቻ ሳይሆን ግጭቱ ሊስፋፋ በሚችልባቸው ሌሎች አካባቢዎችም የበለጠ ዘላቂ መረጋጋት እንዲኖር ያስችላል ሲሉም ጠቁመዋል።በቡድን-7 የጋራ መግለጫ፥ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት እየጨመረ መምጣቱን በመጥቀስ፤ እየታዬ ያለው መካረር የትኛውንም ሀገር ወይም ህዝብ አያተርፍም ሲል አስገንዝቧል።
FBC
More Stories
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፑቲን ጋር የሚያደርጉት ንግግር እየተመቻቸ መሆኑን ገለጹ።
የአሜሪካ ኮንግረስ በአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ድምጽ ሰጠ
አስደንጋጩ የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት አልበረደም