January 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሶማሌ ክልል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ


በሶማሌ ክልል በምግብ ሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 57 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያውን ተከትሎ በጅግጅጋ፣ ቀብሪደሀር እና ጎዴ ከተሞች በምግብ ሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

ማሻሻያውን ተከትሎ አንዳንድ ነጋዴዎች በዘይት፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ ስኳር፣ ዱቄት እና ማካሮኒ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን በተደረገ ክትትል ማረጋገጡን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አብዱላሂ አደን ለኢቲቪ ተናግረዋል።

በዚህም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 57 የንግድ ድርጅቶች ሲታሸጉ፤ ከ1 ሺህ 2 መቶ ለሚበልጡ ነጋዴዎችም ግንዛቤ መፍጠር መቻሉን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ያለ በቂ ምክንያት የንግድ ቦታቸውን በመዝጋት እና በመጋዘን በማከማቸት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር አስተዋፅኦ አድርገዋል በተባሉ ድርጅቶች ላይም ከፅሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አመላክተዋል፡፡

በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆመው ቢሮው ነጋዴዎች ከመሰል ድርጊት እንዲቆጠቡም አሳስቧል።

FBC