November 23, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ባንኮች ህልውናን ያስቀጠለ ነው-ጠ/ ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

 የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ባንኮች ህልውናን ያስቀጠለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ትናንት በሰጡት ማብራሪያ÷ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ዝግ አድርጋ መቆየቷ ለዘመናት ፈተና ውስጥ እንድትወድቅ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም የወጪ ንግዱ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሬ ማስገባት ተስኖት መቆየቱን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ምርቶችም በኮንትሮባንድ እንዲወጡ ማድረጉን ነው ያነሱት፡፡

ኢትዮጵያ ባላት አቅም ልክ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለችም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የጥቁር ገበያ ስርዓት እንዲስፋፋ በማድረግ የዋጋ ንረት በዜጎች ላይ ጫና እንዲፈጥር ማድረጉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

ከዚህ አኳያ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ የተጫኑ ስብራቶችን በማንሳት የተሻለ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የፋይናንስ ሴክተሩን ህልውና በማስቀጠል ረገድም ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቦንድ ግዥ ያሰባሰበውን ገንዘብ ብድራቸውን መመለስ ላልቻሉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ይህም ባንኩን ባለ እዳ እንደሚያደርገውና እዳውን መመለስ ካልቻለ ደግሞ መፍረሱ አይቀሬ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መፍረስ ኢትዮጵያውያን በባንኮች ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚያሳጣ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህም የሀገር ውስጥ ባንኮችን በገበያው የመቀጠል እድላቸውን አዳጋች ያደርገው እንደነበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) እና ከዓለም ባንክ ጋር ባደረጋቸው ድርድሮች ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚመለከት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በድርድሩም ባንኩ 700 ሚሊየን ዶላር የሚሆን ተጨማሪ ገንዘብ ከተቋማቱ ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡

ይህም የባንኩን ህልውና ያስቀጠለ ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ ልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ እንደሚያስቀጥልም ተናግረዋል፡፡

FBC

You may have missed