October 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሀገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞች በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ እንደሚገባቸው ተገለጸ

በሀገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማሳወቅ ባሻገር በሂደቱ በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ እንደሚገባቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለፀ፡፡የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ጋር በመተባበር በምክክሩ ሂደት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ ሁለተኛው ዙር አገር አቀፍ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና በሀሳብ መሪዎች መካከል የሚስተዋሉ መሠረታዊ የሆኑ ልዩነቶችንና ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በአዋጅ የተቋቋመው ኮሚሽኑ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።ሀገሪቱ በሚያጋጥሟት ግጭቶች አካል ጉዳተኞች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች በመሆናቸው ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ሂደት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል። በመሆኑም በምክክሩ አካል ጉዳተኞች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማሳወቅ ባሻገር በሂደቱ በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ እንደሚገባቸው ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ከ23 ሚሊዮን በላይ የሆኑ የአካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ ጠቁመው በሀገሪቱ በሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሁሉም ማህበረሰብ ተጎጅ ቢሆንም አካል ጉዳተኞች ግን የከፋ ተጎጂ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ችግሮችን በምክክር በመፍታት ሂደት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።የምክክር መድረኩ ተሳታፊ የአካል የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ውይይት የመፍታት ባህል እንዲያዳብሩ አሳስቧል። በመድረኩ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የተወጣጡ ተወካዮች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

EBC