January 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሞሮኮ ወታደራዊ ልዑክ ጋር ተወያዩ

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሞሮኮ ወታደራዊ ልዑክ ጋር ተወያዩ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሞሮኮ ወታደራዊ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡ ፊልድ ማርሻሉ በሞሮኮው ምክትል ኢንስፔክተር ጀኔራል ስታፍ ሜጄር ጄኔራል አዚዝ ኢድሪሲ የሚመራ ወታደራዊ ልዑክን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ በውይይቱም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ግንኙነቱ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ “አሁን የተዘጋውን በር ከፍተን አዲስ የግንኙነት መስመር ለመዘርጋት ውይይት እና ጉብኝት ማድረጉ መልካም ነገር ነውና እጅግ ደስተኞች ነን” ብለዋል፡፡ ሜጄር ጀኔራል አዚዝ እድሪሲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበርም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ግዳጁን በብቃት መወጣት የሚችል ጠንካራ ወታደር ያላት ሀገር መሆኑን ተናግረዋል። ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በአዲስ መልክ ለማደስ እና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን በሞሮኮ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን በሚቀጥሉት ተከተታይ ቀናት የሞሮኮው ወታደራዊ ልዑክም በተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች በመዘዋወር ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋል፡፡ከጉብኝቱ በኋላ የሚደረገው የሃሳብ ልውውጥ እና ውይይት ቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካካል ለሚደረገው ወታደራዊ ስምምነት እና የአፍሪካዊ ወንድማማችነት መንፈስ ታላቅ መሰረት ይጥላል ሲሉ ውይይቱን የተካፈሉት የመከላከያ ውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ መናገራቸውን የመከላከያ ሠራዊት የማህበራዊ የትስስር ገጽ ዋብ በማድረግ EBC ዘግቧል።