November 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በህንድ ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓት ላይ በተፈጠረ መተፋፈግ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 121 ደረሰ

በሰሜናዊ ህንድ በሂንዱ ሀይማኖታዊ ፌስቲቫል ላይ በተፈጠረ መተፋፈግ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 121 መድረሱ ተገለፀ፡፡

አደጋው በህንድ ኡታር ፓራዴሽ ግዛት ሀታራስ በተባለው ስፍራ ላይ የሂንዱ እምነት ተከታዮች ሀይማታዊ ስነ ስርዓት እያከናወኑ በነበረበት ወቅት የተፈጠረ ስለመሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

ከሟቾቹ ውስጥ ሴቶች እና ህፃናት እንደሚገኙበት የተገለፀ ሲሆን ተጎጂዎችን ወደ ህክምና የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከአካባቢው በወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደታየውም በሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቱ ላይ በተፈጠረ መተፋፈግ በርካታ ሰዎች በመንገድ ዳርቻዎች ወድቀው ታይተዋል።

የአደጋው መንስኤ እስካሁን አለመታወቁ የተገለፀ ሲሆን የፓራዴሽ ግዛት ፖሊስ ስለ ክስተቱ ዝርዝር መግለጫ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል።

ፌስቲቫሉን ለመታደም ለ80 ሺህ ሰዎች ፈቃድ ቢሰጥም በስፍራው የተሰባሰቡት ሰዎች ቁጥር 250 ሺህ ያህል እንደሆነ ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።

ቀደም ሲል በፈረንጆቹ 2013 በሂንዱ ፌስቲቫል ላይ በተፈጠረ ግጭት 115 ሰዎቸ ሲሞቱ በተመሳሳይ በ2018 በሂንዱ ፌስቲቫል ተሳታፊዎች ላይ በደረሰ የባቡር አደጋ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ዘገባው አስታውሷል።

FBC