መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ከመጠበቅ ባሻገር ለሀገሪቱ ስፖርት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ሌተናል ጀነራል አለምሸት ደግፌ ተናግረዋል፡፡ መቻል የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ያስጠሩ ድንቅ ስፖርተኞች መፍለቂያ መሆኑንም ሌተናል ጀነራሉ ገልጸዋል፡፡ መነሻውን እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው “መቻል ለኢትዮጵያ” የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል። “ስፖርት ጤናማ እና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር ወሳኝ ነው” ያሉት የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ሃላፊ ሌተናል ጀነራል አለምሸት ደግፌ፤ በኦሎምፒክ የመጀመሪያ ወርቅ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ያስገኘው ሻምበል አበበ ቢቂላ የመቻል ስፖርት ክለብ ትሩፋት እንደሆነ ጠቀሰዋል። ኢትዮጵያ በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት ውድድር መድረኮች ለተቀዳጀቻቸው ድሎችም መቻል ስፖርት ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከተ አስታውሰዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ባሻገር የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ ብርቅዬ አትሌቶችን እና እግር ኳስ ተጫዋቾችን ያፈራ ተቋም መሆኑንም ጠቅሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል። የመቻል 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል ::
EBC
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።