June 30, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የለምጽ ምንነት እና ህክምናው

 ለምጽ (vitiligo) በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ የቆዳ ቀለም እንዲነጣ የሚያደርግ በሽታ ነው፡፡

በበሽታው የተጠቃ የቆዳ ክፍል በጊዜ ሂደት ስፋቱን እየጨመረ ሊሄድ ይችላል፤ ሕመሙም ከውጭኛው ቆዳ በተጨማሪም ፀጉር እና የአፍ እና የብልት የውስጥ ክፍልን ሊያጠቃ ይችላል፡፡

ለምጽ ጥቁር ቆዳ ባላቸው ሰዎች ላይ የበለጠ በግልፅ ይታያል ይህ ማለት ግን ነጭ ቆዳ ያላቸውን አያጠቃም ማለት አይደለም፡፡

ለምጽ በማንኛውም ዕድሜ ክልል ውስጥ ሊከሰት የሚችል ሲሆን÷ የቆዳ ንጣቱ እየጨመረ ሲመጣ ወደ ሐኪም ቀርቦ መታየት ያስፈልጋል፡፡

ለምጽ ፈውስ ባይኖረውም፤ መስፋፋትን የሚቀንሱ ወይም የቆዳ ቀለምን ወደነበረበት ለመመለስ የሚረዱ ሕክምናዎች አሉ።

የለምጽ መንሥኤዎች ምንድናቸው?

መንስዔው በትክክል አይታወቅም፤ ነገር ግን የሰውነት በሽታ የመከላከያ ስርዓት የራስን የቆዳ ቀለም አምራች ህዋሳትን በሚያጠቃበት ጊዜ የሚከሰት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

በዚህም ምክንያት ለምጽ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሚከሰቱ ሌሎች ህመሞች ጋር ተያያዥነት አለው ተብሎ ይታሰባል፤ ለምሳሌ የስኳርና የእንቅርት ህመም እንዲሁም ላሽ ይጠቀሳሉ፡፡

ለምጽ ከጭንቀት፣ ከእርግዝና እንዲሁም ከአደጋ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል፤ ለከባድ ፀሐይ ጨረር መጋለጥ ወይም የቆዳ ቁስለት የመሳሰሉ ነገሮች ሕመሙን ሊቀሰቅሱ ይችላል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የለምጽ በሽታ በዘር እና በንኪኪ አይተላለፍም፡፡

የለምጽ ምልክቶች ምንድናቸው?

የለምጽ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ በእጅ፣ በፊት እና በብልት አካባቢዎች ላይ ይታያል፤ የራስ ፀጉር፣ ቅንድብ ወይም ጺም ላይ ያለጊዜው መንጣት ወይም ሽበት ይታይበታል፡፡

የለምጽ ሕክምና ምንድነው?

በመጀመሪያ ስፋት ለሌላቸው የቆዳ ክፍሎች የተለያዩ የሚቀቡ መድሃኒቶች አሉ::

ብርሃንን መሠረት ያደረጉ ሕክምናዎች የቆዳ ቀለምን ለማደስ ይረዳሉ፤ በመድኃኒት፣ በብርሃን ወይም በቀዶ ጥገና ሕክምና ወራት ሊፈጅ እንደሚችል ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

እስካሁን ድረስ የለምጽ ሂደትን ሊያስቆም የሚችል መድኃኒት ባይገኝም አንዳንድ መድኃኒቶች በብቸኝነት ወይም ከብርሃን ሕክምና ጋር በጥምር ጥቅም ላይ ሲውሉ የቆዳ ቀለሞች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ይረዳሉ፡፡

FBC