January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ልኬት በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት መከናወኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ልኬት አሁን ያለበት ሁኔታ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት መከናወኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ገለጹ፡፡የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ቅድመ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ከቀናት በፊት ሲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገሪቱ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም፤ የኢትዮጵያ የደን ልማት ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በመሆን አሁን ያለበት ሁኔታ መጠናቱን ተናግረዋል።በጥናቱ ዓለም አቀፍ የደን ምርምር ማዕከል፣ ሴንተር ፎር ትሮፒካል አግሪካልቸር፣ ወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጅኦ ስፓሻል ኢንስቲቱት የተሳተፉ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።የጥናቱ ሂደት የተካሄደው በተመባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን መስፈርት መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል።መስፈርቶቹ ዛፎች ያረፉበት መሬት ስፋት ከ500 ካሬ ሜትር የማያንስ፣ ቁመታቸው ከሁለት ሜትር የማያንስ እና ቅርንጫፎቻቸው የሚሸፍነው መሬት ከ10 በመቶ የማያንስ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል።በመስፈርቶቹ መሰረት ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የደን ሽፋን ልኬት መስፈርት በተመባበሩት መንግስታት ድርጀት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን ተቀባይነት ማግኘቱን አስታውሰዋል፡፡በነዚህ መስፈርቶች መሰረት በተደረገ የደን ሽፋን ልኬት አሁን ላይ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ማረጋገጥ ተችሏል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።የደን ሽፋኑ ሲሰላ ዘመኑ የደረሰበት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ትግበራ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰው፤ ከፍተኛ የጂአይኤስ እና የሪሞት ሴንሲንግ እውቀት ያላቸው ባላሙያዎች መሳተፋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

FBC