January 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የሚኒስትሮች ም/ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 36ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-

1. በመጀመሪያ ምክር ቤቱ የተወያየው የአለም አቀፍ አቪዬሽን ኮንቬንሽንን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የኮንቬንሽኑ መሻሻል ለሀገራችን ጥቅሞች መከበርና በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚኖራትን የውክልናና ተሰሚነት ዕድል የሚያሰፋ እንዲሁም የሀገራችንን የሲቪል አቪዬሽን መዋቅር ዓለማቀፍ እውቅና ለማጉላት የሚረዳ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ አደጋ የመድን ፖሊሲ የአረቦን ተመን እና የካሳ መጠን ከፍያን ለመወሰን በወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ለማስቻል፣ የአዋጁን ተፈፃሚነት ለማጠናከር፣ ለሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ አደጋ የመድን ፖሊሲ የሚከፈለውን የአረቦን ተመን እና የካሳ መጠን ለመወሰን እንዲሁም አዲስ ወደ ኢንዱስትሪው ለተቀላቀሉ በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ተመጣጣኝ የሶስተኛ ወገን መድህን ሽፋን አረቦን ተመን አካቶ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክን ለመቆጣጠር በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡
የመንገድ ትራፊክ አደጋ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚነካ እንደመሆኑ መጠን በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ለመከላከል እንዲቻል ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ላይ ነው፡፡ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ዜጎችና በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በፍትሐዊነት ለማዳረስ አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር እና የትምህርትን ጥራት፣ ተደራሽነት እና ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ህግ ማውጣት በማስፈለጉ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
አዋጁ ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት አግባብነትን፣ ሥርዓተ ትምህርትን፣ የትምህርት ተቋማት አደረጃጀትን እና መምህራንን የሚመለከቱ ሙያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን እንዲሁም የትምህርት ተቋማት ደረጃ ማውጣትን እና ከመንግሥት ውጭ ባሉ የትምህርት ተቋማት ላይ የሚደረግ ቁጥጥርን በተመለከተ ድንጋጌዎችን አካቶ የቀረበ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ የትምህርት ብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍን ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይነው፡፡ በአገሪቱ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጡ የብቃት ማረጋገጫዎችን ምደባ፣ ዝግጅት፣ ትግበራና ምዘና ላይ ጥራትን በማረጋገጥ እንዲሁም በብቃት ማረጋገጫዎች መካከል ተነፃፃሪነት እና ሽግግርን ለማከናወን የሚያስችል ስርአት መዘርጋት በማስፈለጉ፤ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ የጥራት መስፈርቶችን እና ስታንዳርዶችን ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

FBC