July 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በረቂቅ አዋጁ ላይ ይበልጥ ግልፅ መደረግ አለባቸው በተባሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደረገ

በፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ ይበልጥ ግልፅ መደረግ አለባቸው በተባሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የውይይቱን አስፈላጊነት ሲገልጹ ረቂቅ አዋጁ በሀገሪቱ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ይበልጥ የሚያሳልጥ እና ሪፎርሙ ወደ ኋላ እንዳይመለስ የሚያደርግ በመሆኑ ትኩረት እንዲያገኝ ነው ብለዋል፡፡ጥያቄው የመጣው ‹‹የመንግስት አገልግሎት በአግባቡ ማግኘት አልቻልኩም›› ከሚለው ህዝብ ነው ያሉት የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፤ ስለሆነም መንግስት እንደ መንግስት የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ በርካታ ችግር የነበረበትን የሲቪል ሰርቪስ አሰራሩን፣ አመራሩን፣ አስተሳሰቡን እና ቴክኖሎጂውን በመቀየር ህዝብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉም ነው ያስገነዘቡት፡፡ሪፎርም ማለት የነበረውን ኋላቀር አሰራር አስጠብቆ ማስቀጠል ሳይሆን የተሻለ ነገር ማምጣት ነው ያሉት የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፤ በሪፎርሙ ለሀገርና ለመጪው ትውልድ ጠንካራ ተቋምና አሰራር መገንባት የሚያስችል መሰረት መጣል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡በዚህ ሂደት ግን የግለሰቦች መብት ያለአግባብ እንዳይጎዳ ሚዛኑን አስጠብቆ በመሄዱ ረገድ ተገቢውን ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡ስለሆነም መንግስት የጀመረው የሪፎርም ስራ እንዲሳካ እና በሲቪል ሰርቪሱ በኩል የሚታዩ ችግሮች ተቀርፈው ህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ምክር ቤቱም ሆነ የሚመለከተው ማንኛውም አካል ለተፈጻሚነቱ ተገቢውን ትኩረትና ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡በመጨረሻም የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ቋሚ ኮሚቴው በውይይቱ ግልፀኝነት የተፈጠረባቸውን ነጥቦች በመውሰድና በመወያየት ረቂቅ አዋጁን ይበልጥ ማዳበር እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው በረቂቅ አዋጁ ላይ የአስረጂ መድረክ እና ይፋ የህዝብ ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ይሁን እንጂ የረቂቅ አዋጁን ይዘት በአግባቡ ባለመረዳት በአንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ጭምር የተዛቡ መረጃዎች እየተላለፉ በመሆኑ ይበልጥ ግልፀኝነት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በመወያየት ረቂቅ አዋጁን የበለጠ ለማዳበር እና ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ለማድረግ ውይይቱን ማድረግ እንዳስፈለገ አስረድተዋል፡፡በውይይቱ ላይም በረቂቅ አዋጁ ላይ ይበልጥ ግልፅ መደረግ አለባቸው በሚል በቀረቡት ሀሳቦች ላይ የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ከቀረቡት ውስጥ ረቂቅ አዋጁ የተለየ የስራ ባህሪ ያላቸውና በአዋጅና በደንብ ስልጣን የተሰጣቸው ተቋማት መብት አይጋፋም ወይ? የሚለው ይገኝበታል፡፡ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ለቀረበው ጥያቄ ሲመልሱ፤ የሪፎርም ስራ ዋነኛው ዓላማ ወጥነት ያለው የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና በረቂቅ አዋጁ ላይም ከተጠቀሱት እንደ ፍርድ ቤት፣ አቃቤ ህግ፣ ፖሊስ፣ መከላከያ፣ እና ደህንነትን ከመሳሰሉ ተቋማት ውጪ ያሉ ተቋማት ወደ ተመሳሳይ ደረጃ እንዲመጡ ለማድረግ መቀመጡን ገልፀዋል፡፡ይሁን እንጂ የተለየ የስራ ባህሪ ያላቸውና በአዋጅና በደንብ ስልጣን የተሰጣቸው ተቋማት የሽግግር ጊዜ እንደሚሰጣቸውና ጥናት በማድረግ በነበሩበት እንዲቀጥሉ ወይም በአዋጁ እንዲካተቱ እንደሚደረግ ምላሽ መስጠታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡