በቤንች ሸኮ ዞን በሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ነጻ የወባ ወረርሽኝ በሽታ የምርመራና ህክምና አገልግሎት መጀመሩን የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል፡፡
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ምናሴ እንደገለፁት ህብረተሰቡ የህመም ስሜት ሲሰማው በአቅራቢያ በሚገኝ የመንግስት የጤና ተቋማት እና ጊዜያዊ የህክምና ጣቢያዎች በመቅረብ ነጻ የወባ ወረርሽኝ ህክምና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የወባ ወረርሽኝ በሽታን ለመግታት ሌሎች የመከላከያ መንገዶችን ላይ ባለድርሻ አካላት ትኩረት በመስጠትና ቁርጠኛ ሆኖ ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የወባ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ መሆኑን ጠቁመው ከክልል እስከ ቀበሌ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ ኤልያስ አያይዘዉም በቤንች ሸኮ ዞን በስድስት ወረዳዎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ነጻ የወባ ወረርሽኝ በሽታ የምርመራና የህክምና አገልግሎት መጀመሩን ጠቅሰዉ በሚዛን አማን ከተማ ከተማ ድንኳን በመዝርጋትም አገልግሎቱ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡
አክለዉም በሌሎች ወረዳዎችም በጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች የምርመራና የህክምና አገልግሎት መጀመሩን ተናግረዉ ህብረተሰቡ የህመም ስሜት ሲሰማዉ በአቅራቢያዉ በሚገኝ የመንግስት ተቋማት እና ግዜያዊ የህክምና ጣቢያዎች በመቅረብ ነጻ የወባ ወረርሽኝ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
ነጻ የወባ ወረርሽኝ በሽታ የምርመራና ህክምና አገልግሎት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ ሳይሆን በበሽታዉ የተጠቁትን ብቻ ሲሆን አንዳንድ ግለሰቦች ህመም ሳይሰማቸዉ በሽታ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ በመቅረብ የሀኪሞችን ጊዜ እየተሻሙ መሆኑንም ጨምረዉ ተናግረዋል፡፡
የወባ ወረርሽኝ በሽታን ለመግታትሸየመከላከያ መንገዶችን ላይ ትኩረት በመስጠትና ቁርጠኛ በመሆን መስራት ስለሚያስፈልግ የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የማህበረሰብ አንቂዎች ፣ የጤና ባለሙያዎች ፣ ወጣቶችና ሴቶች ወቅቱ ለወባ አመቺ በመሆኑ በየመንደራቸዉ በመዉጣት አካባቢን ማጽዳት እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል፡፡
የህክምናዉ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ያነጋገርናቸዉ አቶ ቡሾ ቢረጋ እና አቶ ምስጋና እሴይ እንዳሉት ምርመራና ህክምናዉ በአቅራቢያችን በመሰጠቱ ደስ ብሎናል ብለዉ በየመንደሩ መሰጠት ቢችል በከፍተኛ ታመዉ በአልጋ የሚገኙ ሰዎችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቅሰዋል፡፡
የወባ በሽታን የመከላከል ስራዎችን በየመንደራቸዉ እየሰሩ ቢሆንም በሽታዉ ከጊዜ እየጨመረ መሄዱን የሚጠቅሱት አስተያየት ሰጪዎች የጤና ባለሙያዎች ክትትል እያደረጉ መሆናቸዉንም አስረድተዋል፡፡
ህክምናዉን ቀደም ባሉት ጊዜያት በጤና ተቋማት ሂደዉ ምርመራና ህክምና ቢያገኙም የመድሐኒት እጥረት መኖር በግል የህክምና ተቋማት ለከፍተኛ ወጪዎች መዳረጋቸዉን የዘገበው የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነዉ።
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።