July 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች – አቶ አደም ፋራህ

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር በሁሉም ዘርፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።በአቶ አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ ከሰኔ 9 እስከ 12 ቀን2016 በሚካሔደውና “ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር” በሚል መሪ ሃሳብ በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።ከፎረሙ ጎን ለጎን አቶ አደም ፋራህ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ዘርፍ ሚኒስትር ሊዩ ጂንቻዎ ጋር ተወያይተዋል።በውይይታቸውም ÷ አቶ አደም ቻይና በኢትዮጵያ ልማት ላይ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋር ሀገር መሆኗን አስረድተው በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች ባጋጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ቻይና የማይናወጥ አቋም ይዛ እያደረገች ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት አቶ አደም÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የፖለቲካ ወዳጅነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ባለው ብሪክስ አባል ሀገር ለመሆን ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲሳካ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና መንግስት ላደረጉት ድጋፍም አመስግነዋል።ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሰራ ገልጸው÷ ሊዩ ጂንቻዎን ጨምሮ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አመራሮች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።ሊዩ ጂንቻዎ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ማዕከል በመሆኗም ቻይና ከኢትዮጵያም አልፎ ከአፍሪካዊያን ጋር ለሚኖራት ትብብር ቁልፍ ሚና እንዳላት አስረድተዋል።በመሆኑም የሁለቱን ሃገራት የቆየ ትብብር ከማሳደግ ባለፈ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱን በልምድ ልውውጥ፣ በስልጠና ፕሮግራሞች እና በአቅም ግንባታ ዘርፍም አጠናክረው መቀጠል እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ከዚህ ባለፈም በንግድና ኢንቨስትመንት ያለውንየሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ቻይና በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸው÷ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ትብብር የተገነባውን የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር በአብነት ጠቅሰዋል።ሚኒስትሩ በመጨረሻም በመጪው ጥቅምት በሚካሔደው የቻይና አፍሪካ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን እንዲገኙ ጋብዘዋል፡፡

FBC