November 8, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢድ አል አደሃ አረፋ በዓልን የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ማሳለፍ ይገባል- የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት

ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓልን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና ያለውን በማካፈል መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ መላውን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 445ኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል አደረሳችሁ ሲል መልዕክት አስተላልፏል::

መልካም ምኞቱ ባስተላለፈበት መግለጫው ሙስሊሙ ህብረተሰብ በዓሉን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብና ያለውን በማካፈል እንዲሆን አስገንዝቧል።

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በሰጡት መግለጫ፤ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ወገኖችን፣ አቅመ ደካሞችንና አሳዳጊ የሌላቸውን ህጻናት በመደገፍ እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንደዚሁም ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር አንድነቱንና ወንድማማችነቱን በሚያጠናክር መልክ በዓሉን ማሳለፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አያይዘዉም በመካሄድ ላይ በሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ህዝበ ሙስሊሙ ንቁ ተሳትፎና ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ምክክሩ በኢትዮጵያ ታሪክ የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት ለህዝበ ሙስሊሙ ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም መከበር መልካም አጋጣሚ የሚያስገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢድ አል አረፋ በዓል ከፆምና ፀሎት ሀይማኖታዊ ሥርዓት በኋላ የሚከናወንና በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዓሉ አላህ የነብዩ ኢብራሂምን ፍቅርና እምነት ፍጹምነትን ለማስተማር ልጃቸውን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ ያዘዘበት፤ እርሳቸውም ለፈጣሪ የነበራቸው እምነትና ፍቅር ጥግ በሚያሳይ ፍጹምነት የሚወዱት ልጃቸውን እስማኤልን ወደ መሰዊያው ያቀረቡበት መታሰቢያ በዓል ነው።

ፈጣሪም በልጃቸው ምትክ ለመስዋዕትነት የበግ ሙክት የተካላቸው መሆኑ የሚታወስበት በዓል ነው፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ዕለቱ የዕርድ ወይም የኡዱህያ ቀን ተብሎ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።

FBC