የ40 አመቱ ግብ ጠባቂ ቻይና ለ2026ቱ የአለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ እንድታልፍ አግዟል በሚል ነው ደጋፊዎቹ ገንዘብ እየላኩ የሚገኙት
1 ነጥብ 4 ቢሊየን ህዝብ ያላት ቻይና ብቸኛው የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋ በ2002 እንደነበር ይታወሳል
የሲንጋፖር ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂው ሃሰን ሰኒ በቻይናውያን የእግርኳስ ደጋፊዎች እየተወደሰ ነው።
ደጋፊዎች “ጀግናችን” ላሉት ሰኒ ገንዘብ በመላክ አድናቆታቸውን እየገለጹለት መሆኑም ተሰምቷል።
የ40 አመቱ ግብ ጠባቂ ከሶስት ቀናት በፊት ያሳየው ብቃት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ህዝብ ያላትን ቻይና ለ2026ቱ የአለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር እንድታልፍ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል።
በምድብ ሶስት ከደቡብ ኮሪያ፣ ታይላንድ እና ሲንጋፖር ጋር የተደለደለችው ቻይና ለመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ለማለፍ የሰን ሁንግ ሚን ሀገርን ደቡብ ኮሪያ ማሸነፍ አልያም ነጥብ መጋራት ይጠበቅባት ነበር።
ባለፈው ማክሰኞ በሴኡል የተደረገው ጨዋታ ግን በደቡብ ኮሪያ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ይህን ተከትሎም የቤጂንግ ተስፋ ተመናምኖ የነበረ ቢሆንም የሲንጋፖሩ ግብ ጠባቂ ብቃት ታድጓቸዋል።
ሲንጋፖርን በባንኮክ ያስተናገደችው ታይላንድ በሶስት የግብ ልዩነት ካሸነፈች ሁለተኛ ሆና ማለፍ ትችል ነበር።
ይህን ለማሳካት ተቃርበው የነበሩት የታይላንድ ተጫዋቾች ሶስት ጎሎችን ቢያስቆጥሩም ሲንጋፖር አንድ ጎል አስቆጥራ 3 ለ 1 በመጠናቀቁ ቻይና ለሶስተኛው ዙር ማጣሪያ አልፋለች።
በባንኮኩ ጨዋታ የሲንጋፖር ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂው ሀሰን ሰኒ 11 ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማምከን የጨዋታው ኮከብ ሆኗል።
ይህን ተከትሎም ቻይናውያን የእግርኳስ ደጋፊዎች ለሰኒ በአካውንቱ ገንዘብ እየላኩ መሆኑን ግብ ጠባቂው ከሲንጋፖሩ ሲኤንኤ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።
ደጋፊዎቹ ሰኒ በከፈተው ምግብ ቤት የተለጠፈ የሂሳብ ቁጥርን በኦንላይን እንዲሰራጭ በመደረጉ ምን ያህል እንደሆነ ያልጠቀሰው ገንዘብ እንደገባለትም ነው የገለጸው።
“ሲጀመር አካባቢ ደስ እያለኝ ነበር፤ በሂደት ግን ህጋዊነቱና መቼ ነው የሚቆመው የሚለው እያሳሰበኝ መጣ” ያለው ግብ ጠባቂው፥ የቻይና እግርኳስ ደጋፊዎች ገንዘብ እንዳያስተላልፉት ጠይቋል።
በሲንጋፖር ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙ ቻይናውያን የሀሰን ሰኒ ምግብ ቤትን አጨናንቀውት በትናንትናው እለት በርካቶች ምግብ አልቋል ተብለው መመለሳቸውንም የሲንጋፖር መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ቻይና ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በ2002 በጋራ ባዘጋጁት የአለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ ከምድቧ ምንም ጎል ሳታስቆጥርና ሁሉንም ጨዋታዎች ተሸንፋ መሰናበቷ ይታወሳል።
የሀገሪቱ እግኳስ አፍቃሪዎች ለሲንጋፖሩ ግብ ጠባቂ ያሳዩት ድጋፍም ቤጂንግ በአለም ዋንጫ የመሳተፍ ፍላጎቷ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል ተብሏል።
Al-Ain
More Stories
ሩድ ቫንኒስትሮይ ከማንችስተር ዩናይትድ ተሰናበተ
የአለም የማራቶን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችው ሩት ቼፕንጌቲች የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የክብር እንግዳ ትሆናለች
ኢትዮጵያና ዑጋንዳ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ