July 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ምክክር ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ትኩረት የሚሰጣቸው አበይት ጉዳዮች፡-

 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የምክክር ምዕራፍ አጀንዳ መሰብሰቡ የሚታወቅ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በቀጣይም ይህንን ሒደት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እያከናወነ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ሒደቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተከናወነ እንደመሆኑ ለስኬቱ ኮሚሽኑ የተለያዩ ትኩረት የሚያሻቸውን ጉዳዮች በመለየት ሥዎችን እየሰራ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡

1. አካታችነት እና ወካይነት

ኮሚሽኑ በጀመረው የምክክር ምዕራፍ በበርካታ ቡድኖች፣ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ተቋማት እና ግለሰቦች የሚቀነቀኑ የተለያዩ ሀሳቦችን በተገቢው መንገድ በማካተት ለሒደቱ ስኬት እየሰራ ይገኛል፡፡

በሒደቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ወኪሎቻቸውን በመላክ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ እንዲንፀባረቅላቸው የሚፈልጓቸውን ሀሳቦች የማቅረብ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡

2. የባለድርሻ አካላትን ሃይል ማመጣጠን

ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት የተለያየ የሃይል ሚዛን ያላቸውን ባለድርሻ አካላት እያሳተፈ እንደሚገኝ ዕሙን ነው፡፡

ይህንኑ መነሻ በማድረግ የተለያየ የሀይል ሚዛን ያላቸውን አካላት በእኩልነት እንደ ባለድርሻ አካል በመቁጠር ሒደቱን እየመራና እያስተባበረ ይገኛል፡፡

3. የሚቃረኑ ፍላጎቶችን ማስተናገድ

ኮሚሽኑ በሚመራው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት እጅግ በርካታ ሃሳቦች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳነት እየመጡ ይገኛሉ፡፡ ባለድርሻ አካላቱ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን ሲያደራጁ በርካታ የሀሳብ ፍጭት ውስጥ ገብተው የተለያዩ ፍላጎቶችን እያንፀባረቁ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ኮሚሽኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሀሳብ በእኩልነት የማስተናገድ ሀላፊነት ያለበት በመሆኑ ሀሳቦችን እንደአመጣጣቸው በአጀንዳነት ያስተናግዳል፡፡

4. ግልፅነት እና ህጋዊነት

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ሒደቱን የሚመለከቱ መረጃዎችን እንደ አስፈላጊነቱ ግልፅ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ ባሻገር ለሒደቱ ህጋዊነት የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን አዘጋጅቶ እና በኮሚሽነሮች ምክር ቤት አስፀድቆ ሂደቱን ማስተባበር ጀምሯል፡፡

መረጃው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው፣

FBC