January 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለባት ተረጋገጠ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ምንም አይነት የደህንነት ስጋት የሌለበት መሆኑ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ተረጋገጠ።

በዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ደህንነት ድርጅት ለ10 ቀናት የተደረገው የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ደህንነት ኦዲት ተጠናቋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑ ተረጋግጧል።

ከ12 አመታት በኋላ የተካሄደው ኦዲት ዛሬ ውጤቱ ይፋ መሆኑን በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምርያ ዳይሬክተር አስራት ቀጀላ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ኦዲቱ በስምንት ወሳኝ ዘርፎች እንደተካሄደ ጠቅሰው÷ በሁሉም ዘርፎች ደህንነቱ የተጠበቀ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በኤርፖርቶችና በህግ ማዕቀፍ ሁለንተናዊ ቅኝቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በአይካኦ የተደረገው የአቪዬሽን ደህንነት ኦዲት ውጤቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ማመላከቻ መሆኑም ተጠቅሷል።

ግኝቱ የኢትዮጵያን ቀደምት ስምና ታሪኳን የሚመጥን መሆኑን በመግለጽ ይህም በአቪዬሽን ዘርፉ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ትልቅ ዋስትና እንደሆነም ነው ያነሱት።

ለስኬቱ ዕውን መሆን ጉልህ ሚና ያበረከቱ ተቋማት እና አመራሮችንም አመስግነው፤ በዚህ ረገድ ተጨማሪ አቅምን ለመፍጠር ተጠናክረው የሚቀጥሉ ጅምር ስራዎች እንዳሉም አመልክተዋል።

FBC