July 2, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኮንጎ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር በይፋ ሥራ ጀመሩ

 ጁዲት ሱሚንዋ ቱሉካ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ ፈጽመው በይፋ ሥራ ጀምረዋል፡፡

ከቤልጂየም ዩኒቨርሲቲ ሊብሬ ዴ ብሬክስልስ በአፕላይድ ኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ቱሉካ፥ ከፈረንጆቹ 2020 እስከ 2023 የፕሬዚዳንት ስትራቴጂክ ክትትል ካውንስል ምክትል አስተባባሪ በመሆን ሲያገለግሉ፤ በ2023 መጋቢት ወር የፕላን ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው መሾማቸው ተገልጿል።

አሁን ደግሞ የሀገሪቱ ምክር ቤት ቱሉካ እና ሌሎች 54 አዳዲስ የመንግስት አስፈጻሚ አባላትን በአብላጫ ድምፅ ካፀደቀ በኋላ በይፋ ስራ መጀመራቸው ተገልጿል።

ቱሉካ በንግግራቸው፥ የመጀመሪያዋ የኮንጎ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ፋና ወጊ በመሆናቸው ኩራት እንደተሰማቸውም ነው የተናገሩት፡፡

ሆኖም የተጣለባቸው ኃላፊነት ቀላል እንዳልሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፥ በኪንሻሳ ወደ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚጠጉ የስራ ዕድልና የሂሳብና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የትምህርት ተቋማትን በመገንባት በማደግ ላይ ባለችው ኮንጎ ጥሩ መሰረት ለመጣል ቃል ገብተዋል፡፡

በተጨማሪም በብሔራዊ ደህንነት፣ በኢኮኖሚ ብዝሃነት፣ በመሰረተ ልማት ትስስር፣ በህዝብ አገልግሎቶች እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እርምጃዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ማለታቸውን የዘገበው ዥኑዋ ነው፡፡

FBC