July 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች መንግሥት ቃልን በተግባር እየፈጸመ መሆኑን ያመላክታሉ- አቶ አደም ፋራህ

በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች መንግሥት ቃልን በተግባር እየፈጸመ መሆኑን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለፁ።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻው የ100 ቀናት የአፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

አቶ አደም ፋራህ ግምገማውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ ገዥው ፓርቲ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለማሳካት ለሕዝብ ቃል የገባቸው ግቦች እንደነበሩት አስታውሰዋል።

በፓርቲው ማኒፌስቶ የተቀመጡ ግቦችን በተግባር ዕውን ለማድረግ የዘንድሮውን ጨምሮ በየጊዜው የአፈጻጸም ግምገማዎች እንደሚደረጉ ጠቁመው÷ በግምገማውም ቃልን በተግባር ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።

ለአብነትም መንግሥት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከአፍሪካ ግዙፍ አምስት ኢኮኖሚዎች አንዱ የማድረግ ግብን ለሕዝብ በይፋ ማሳወቁን አስታውሰዋል፡፡

የጥቅል ሀገራዊ ምርትን በአጭር ጊዜ 205 ቢሊየን ዶላር በማድረስ በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን እንዲሁም በነፍስ ወከፍ ገቢም ዕድገት መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ከ3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በማልማትና 100 ሚሊየን ኩንታል ምርት በመጨመር ምርታማነትን ማሳደግ ስለመቻሉም ገልፀዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ጨምሮ በዘርፉ በተሰሩ ሥራዎች ነባር ኢንዱስትሪዎች ወደ ሙሉ አቅማቸው እንዲሸጋገሩና አዳዲስ አልሚዎችም ወደማምረቻው ዘርፍ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

በቱሪዝምና በማዕድን ዘርፎች ያሉ ዕምቅ ጸጋዎችን የመለየትና የማልማት ሥራ ትላልቅ ኩባንያዎች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማስቻል ለሀገር ብልጽግና የሚበጁ ተግባራት ተከናውነዋልም ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው÷ በግምገማዎቹ ቃልን በተግባር ለማረጋገጥ ጥረቱ መቀጠሉን አመላካች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሕዝባዊ ስብሰባዎች የሚነሱ የሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን በመለየት የመፍታት ቃል አንዱ ቁልፍ ጉዳይ እንደነበር ገልጸው÷ በዚህም ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

FBC