January 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሚቀጥሉት ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት በበልግ ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች ጠቀሜታ ይኖረዋል – ኢንስቲትዩቱ

 በሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት የበልግ እርጥበት ተጠቃሚ በሆኑት አካባቢዎች ዘግይተው ለተዘሩና ፍሬ በመሙላት ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች ጠቀሜታ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

እንዲሁም ለጓሮ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች የውሃ ፍላጎትን ከማሟላት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው የተገለፀው፡፡

በተጨማሪ አስቀድመው ለሚዘሩ የመኸር ሰብሎች ዘር በወቅቱ ለመዝራት እና ማሳ ለማዘጋጀት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡

በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የሚጠበቀው የእርጥበት ሁኔታ የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራትና ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለተተከሉና ለሚተከሉ የዛፍ ችግኞች እድገት የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ነው የተባለው።

በሌላ በኩል በሚቀጥሉት ቀናት በዓባይ፣ በላይኛውና በመካከለኛው ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ አዋሽ እና ተከዜ እንዲሁም በጥቂት የአፋር ደናክል ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የእርጥበት ሁኔታን ያገኛሉ፡፡

ይህም የእርጥበት ሁኔታ በተፋሰሶች ላይ የሚኖረውን የገፀ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር የውሃ ሀብትን ያሻሽላል፤ ለመስኖም ሆነ ለሀይል ማመንጫነት የሚያገለግሉ የግድቦችን የውሃ መጠን ያሻሽላል ብሏል ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ፡፡

FBC