የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና በብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ አቶ ማሞ ምህረቱ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ በሩስያ በጀመረው 3ኛው የብሪክስ የአባል ሀገራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። አቶ ማሞ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በተለዋዋጭ እና ሊተነበይ በማይቻል የዓለም ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ብሪክስ ሀገራትን እና ሃብቶችን በማሰባሰብ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን በአጋርነት መንፈስ ለመቅረፍ አረጋጊ ኃይል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ የብሔራዊ የብሪክስ ተሳትፎ ስትራቴጂን በብሔራዊ የሚኒስትሮች አስተባባሪ ኮሚቴ ማፅደቋን ጨምሮ ወደ ብሪክስ ማዕቀፍ በተሳለጠ ሁኔታ መግባቷን ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎችንም አብራርተዋል። በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪስት ፍሰትና ሌሎች መስኮች ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባ እንዲሁም የልማት ፋይናንስን በመጨመር አካታች እና ዘላቂ ልማትን መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።አዲሱ የልማት ባንክ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ከኢትዮጵያ የልማት ትልሞች ጋር የተጣጣሙ በመሆናቸው ኢትዮጵያ በተቻለ ፍጥነት ወደ ባንኩ ትቀላቀላለች ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል። ስብሰባው ከሰኔ 3-4 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መምከር መቀጠሉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
EBC
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።