July 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የሜታ ኩባንያ ፍልስጤማዊያን የሚያሰራጯቸው መረጃዎችን ተደራሽነት በመገደብ ክስ ቀረበበት

ሜታ ፍልስጤማዊያን ሰራተኞቹ የዘመዶቻቸቸውን ሞት በተመለከተ በገጾቻቸው የሚያጋሯቸውን መረጃዎች እንዲሰረዙ አድርጓል ተብሏልፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የሚያስተዳድረው የሜታ ኩባንያ በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት መረጃዎች ስርጭት ላይ የተለያዩ ክልከላዎችን በማድረግ ክስ ቀርቦበታል፡፡የቀድሞ የተቋሙ ኢንጂነር የነበረው ፍልስጤም አሜሪካዊው ፊራስ ሃማድ ያቀረበው ክስ፤ ሜታ በተለያዩ ገጾች ላይ በፍልስጤማዊያን የሚለጠፉ ይዘቶች ተደራሽነት እንዳይኖራቸው፣ በርካታ ተከታይ ባላቸው ገጾች የጦርነቱን አስከፊነት እና እየደረሱ የሚገኙ ጉዳቶችን የሚያሳዩ ልጥፎች በፍለጋ እንዳይገኙ አድርጓል ሲል ወንጅሏል፡፡በተጨማሪም በተቋሙ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ፍልስጤማዊያን ሰራተኞች የዘመዶቻቸቸውን ሞት በተመለከተ በገጾቻቸው የሚያጋሯቸውን መረጃዎች እንዲሰረዙ እንሚያደርግ፣ የፍልስጤም ሰንደቅአላማ ኢሞጂን ተጠቅመው በገጾቻቸው ሀሳቦችን በሚለጥፉ ሰራተኞቹም ላይ ምርመራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ኩባንያውን በካሊፎርኒያ ፍርድ ቤት የከሰሰው የቀድሞ ሰራተኛ ሀማድ በዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት መሰል ሁኔታዎች እንዳልነበሩ በመረጃ ስርጭቶችም ላይ እገዳ እናዳልነበር ተናግሮ ይህ እየተደረገ ያለው በፍልስጤማዊያን ብቻ ላይ ነው ብሏል፡፡ባሳለፍነው ህዳር ከሜታ ሰራተኘነቱ የተሰናበተው ሀማድ ከስራ የተባረርኩት በፍልስጤማዊው የፎቶ ጋዜጠኛ ሞታዝ አዚዝ ተቀርጾ በኢንስታግራም ላይ የተለጠፈውን ተንቀሳቃሽ ምስል ክልከላ እንዲስተካከል በማድረጉ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በጋዛ የፈራረሱ ህንጻዎችን የሚያሳይ ቢሆንም ወሲባዊ ይዘት ያለው ምስል በሚል ኢንስታግራም እንዳይዳረስ ተከልክሎ እንደተመለከተ እና ምስሉ ከወሲባዊ ጉዳይ ጋር ምንም የሚያገናኝው ነገር ባለመኖሩ ክልከላው እንዲነሳ ማድረጉን ነው የተናገረው፡፡ ይህን ተከትሎ በተቋሙ ምርመራ ሲደረግበት የነበረው ሰራተኛው የተቋሙን ፖሊሲ ጥሰሀል ተብሎ ከሰራ መሰናበቱን ሮይተርስ አስነብቧል። ሜታ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ፍልስጤማዊያንን የሚደግፉ ይዘቶች እንዳይሰራጩ አግቷል በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡ በቅርቡም 200 የሚደርሱ የተቋሙ ሰራተኞች ለዋና ስራ አስፈጻሚው ማርክዙከርበርግ እና ሌሎች ሃላፊዎች በግልጽ በጻፉት ደብዳቤ ይህንኑ ቅሬታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ ፌስ ቡክ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት የሚያባብሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ አመጽ እና ግጭት የሚያነሳሱ ጽሁፎችን አይቶ እንዳላየ አልፏል በሚል ተከሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡በተጨማሪም ፌስቡክ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ማይናማር፣ ሲሪላንካ፣ ኢንዶኔዢያ እና ካምቦዲያ ስለሚከሰቱ ዘርን መሰረት ያደረጉ ብጥብጦች እና ሀይማኖታዊ ግጭቶች፣ ሲለቀቁ እና ሪፖርት ሲደረግለት በዝምታ በማለፉ የበርካቶች ህይወት ተቀጥፏል በሚል የቢሊዮን ዶላሮች ክስ ቀርቦበት እንደነበር አይዘነጋም።

Al-Ain