July 2, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በኢትዮጵያ በሰላም ወጥቶ መግባት አጠራጣሪ ሆኗል- ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ

በቤተክርስቲያኗና በአገልጋዮቿ ላይ የሚደርሱ በደሎች ቀጥለዋል ብለዋል ፓትርያሪኩ

ቤተክርስቲያኗ አመታዊውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ማካሄድ ጀምራለች

በኢትዮጵያ በሰላም ወጥቶ መግባት አጠራጣሪ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡ 

ፓትሪያሪኩ ይህን ያሉት ዛሬ በተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡

በሀገር ደረጃ እየቀጠለ ያለው አለመግባባት ለጠቅላላ ማህበረሰባችን ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል ያሉት ፓትሪያሪኩ፥ የቤተክርስቲያኗ ፈተና ምንጭ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዕድል ሰጩው ሁኔታ ይህ ሀገራዊ አለመግባባት ነው ብለዋል፡፡

በዚህ አለመግባባት ምክንያት መነኮሳት፤ መምህራን ካህናት፣ ምእመናን፣ አብያተ ክርስቲያናት ከባድ ጉዳት እየደረሰባቸውም ቢሆንም “ይህን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረትም ጎልቶ አይታይም’’ ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት አመታት በቤተክርስቲያኗ እና በአገልጋዮቿ ላይ የሚደርሱ በደሎች አለመቆማቸውን እና ወደፊትም ሊቀጥሉ እንደሚችሉ የገለጹት አቡነ ማትያስ፥ በደልን በካሣ እና በዕርቅ መዝጋት እንዳይደገም ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ፓትሪያሪኩ በመክፈቻ ንግግራቸው ከውጫዊ ችግሮች ባሻገር ቤተክርስቲያኗ የገጠማትን ውስጣዊ ፈተና አንስተዋል።

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የሹመት ፈላጊነት እና የገንዘብ ፍቅር መንገሱን፣ መለያየት እና መነቃቀፍ እየሰፋ መምጣቱን በማንሳትም ኃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮች “በበጎቻችን ዘንድ የነበረንን ተሰሚነት እና ተደማጭነት ሊቀንሱብን እየተንደረደሩ ነው” ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፤ በአገልጋዮች እና ምዕመናንን ላይ የሚደርሱ ግድያዎች እንዲቆሙ ቤተክርስቲያኗ በተደጋጋሚ ማሳሰቧ ይታወሳል።

ቤተክርስቲያኗ ውስጣዊ አንድነቷን አደጋ ላይ ይጥላሉ ባለቻቸው ጉዳዮች ላይም አቋሟን የሚያንጸባርቁ መግለጫዎችን ስታወጣ ቆይታለች።

ባለፈው አመት ጥር ወር ከቤተክርስቲያኗ አፈንግጠው የራሳቸውን ሲኖዶስ አቋቁመናል ካሉ የቀድሞ አባቶች ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን አለመግባባት በስምምነት መቋጨቷ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ በትግራይ ክልል የተከናወነውን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲቆም ጥረት ስታደርግ መቆየቷና ሹመቱ መካሄዷ በእጅጉ እንዳሳዘናት መግለጿም አይዘነጋም።

ቤተክርስቲያኗ ቀኖናዋን ባልጠበቀ መልኩ የኦሮሚያ ሲኖዶስን ከመሰረቱ አባቶች ጋር ስምምነት ላይ መድረሷን ካሳወቀች በኋላም የቤተክርስቲያኗን አንድነት የሚፈታተኑ ድርጊቶች መቀጠላቸውን በመግለጫዎች ስታሳውቅ ቆይታለች፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ የጀመረው እና ለቀናት በሚዘልቀው ምልዓተ ጉባኤው ቤተክርስቲያኗን እየፈተኑ በሚገኙ ሀገራዊ ሁኔታዎች እና ውስጣዊ ችግሮች ዙሪያ መክሮ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ተገልጿል።

Al-Ain