January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ቻይና ከአረብ ሀገራት መሪዎች ጋር በእስራኤል እና ፍልስጤም ጉዳይ ልትመክር ነው

በጉባኤው የአረብ ኢምሬትስ እና የግብጽ ፕሬዝዳንቶች ይሳተፋሉ ተብሏል

መሪዎቹ 10ኛውን የቻይና አረብ ሀገራት ትብብር የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ፎረም መክፈቻ ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡

የአረብ ኢምሬትስ ፣ባህሬን፣ ቱኒዙያ፣እና ግብጽ መሪዎች ይሳተፉበታል የተባለው በእስራኤል እና ጋዛ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚመክረው ጉባኤ ነገ ይጀመራል፡፡

መሪዎቹ በተጨማሪም 10ኛውን የቻይና አረብ ሀገራት ትብብር የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ፎረም መክፈቻ ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የባህሬን ንጉስ ሃማድ ቢን ኢሳ አል ካሊፋ፣ የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንቶች ሸክ ሞሀመድ ሚን ዛይድ አል ናህያን፣ የግብጹ አብድል ፈታህ አልሲሲ እና የቱኒዚያው ካይስ ሳይድ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዥንፒንግ ጋር ይመክራሉ፡፡

ውይይቱ በዋናነት በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ስላለው ጦርነት ትኩረቱን የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም ቀጠናዊ እና አለም አቀፋዊ የጂኦፖለቲክስ ጉዳዮች እንዲሁም በቤጂንግ እና በአረብ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የተመለከቱ አጀንዳዎች ይነሱበታል፡፡

 ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላም በእስራኤል እና ፍልስጤም ጉዳይ ተሳታፊዎቹ የጋራ አቋም እንደሚያወጡም ይጠበቃል ፡፡ 

በሀማስ እና በእስራኤል መካከል የአሸማጋይነት ሚና እንዲኖራት የምትፈልገው ቤጂንግ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከአረቡ አለም ጋር ጠንካራ ወዳጅነትን ለመፍጠር እየሞከረች ትገኛለች፡፡

 የሀገሪቷ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ይ በባለፈው ጥር በአረብ ሀገራት ጉብኝት አድርገው ነበር። በግብጽ በነበራቸው ቆይታም ከአልሲሲ ጋር በጋራ በወጡት መግለጫ በፍልስጤም እና እስራኤል ጉዳይ ሁሉን ያካተተ ዘላቂ የመፍትሄ ሀሳብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ 

ፕሬዝዳንት ሺ ዝንፒንግም አለም አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ እንዲካሄድ ጥያቄ አቅርበዋል፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጋዛ ያለውን ግጭት ለማብረድ ባለፈው ህዳር ከፍልስጤም፣ ከሳኡዲ አረብያ፣ ከግብጽ ከጆርዳን እና ኢንዶኔዥያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጋር መምከራቸው ይታወሳል፡፡

በሀማስ እና በእስራኤል መካከከል የተነሳውን ግጭት ለማስቆም ግብጽን ጨምሮ በተለያዩ የአረብ ሀገራት አሸማጋየነት ተደጋጋሚ ድርድሮች ቢደረጉም በቅደመ ሁኔታዎች መበርከት ምክንያት እስካሁን ፍሬያማ ሊሆኑ አልቻሉም።

Al-Ain