January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

“የአፈር ጤና ለሀገር ህልውና ” በሚል መሪ ቃል የግብርና ኖራ አጠቃቀም ንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው

በንቅናቄው ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የአፈር ጤንነት መጓደል በግብርና ስራዎች ላይ ውጤታማ መሆን እንደማይቻል ተናግረዋል ።

በየወቅቱ የምንተክላቸው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ስራዎች የአፈር ጤንነትን ለማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል ።

የአፈር ጤናማ አለመሆን ችግሮች በሁለት መንገዶች የሚከሰቱ ሲሆን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ መንስኤዎች እንደሚከሰትም ገልጸዋል።

በክልሉ የአፈር አሲዳማነት መጠኑ እየጨመረ በመሆኑ ይህንን ለመከላከል ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት በመስጠት አሳስበዋል ።

በክልሉ ከ863 ሺህ በላይ ሄክታር/ 49.8 ከመቶ መሬት አሲዳማ በመሆኑ በግብርና ስራዎች ላይ ምርታማነትን እየቀነሱ መሆኑንም አመላክተዋል ።

የአፈር አሲዳማነት ችግር ለመከላከል የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ከ100 ሺህ በላይ ኩንታል ኖራ ድጋፍ መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።

የአሲዳማ አፈርን ለመከላከልና ለማከም የባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ርብርብ ወሳኝነት አለው ብለዋል።

በአንድ ሄክታር አሲዳማ አፈር ከ30_50 ኩንታል የግብርና ኖራ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ማስረሻ በላቸው በዚህ ተግባር ራስን ቀይሮ አርሶ አደሩን መቀየር ይገባልም ብለዋል።

የአፈር አሲዳማነት ችግሮችን በተገቢው በመለየት በግብርና ስራዎች ላይ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ስራዎችን በትኩረት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

የግብርና ኖራ አጠቃቀም የንቅናቄ ሰነድ በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት መሬት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ በሆኑት በአቶ ውብሸት ዘነበ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

በቀረበው ሰነድ 2 ሺህ 2 መቶ 68 ሄክታር መሬት በ32 ወረዳዎች በንቅናቄ የግብርና ኖራን በመጠቀም መሬት ይታከማል ሲሉም አቶ ውብሸት ተናግረዋል ።

በንቅናቄው መድረክ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣የክልሉ መንግስት ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ፣የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው ስል የዘገበው የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ነው ።