January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የማሻ ኤፍ ኤም 103.8 ከወረዳ እስከ ሀገሪቱ መዲና በመደመጡ መደሰታቸውን ነዋሪነታቸውን በአዲስአበባ ያደረጉ የአካባቢው ተወላጆች ገለጹ።

በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የማሻ ኤፍ ኤም 103.8 ከወረዳ እስከ ሀገሪቱ መዲና በመደመጡ መደሰታቸውን ነዋሪነታቸውን በአዲስአበባ ያደረጉ የአካባቢው ተወላጆች ገለጹ።

ከወረዳ እስከ ዓለም (Woreda to World ) በሚል መሪ ቃል ከተቋቋመ አጭር ጊዜ የሆነው የማሻ ኤፍ ኤም 103.8 በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ በሸካ ዞን የአካባቢውን ባህል፤ቋንቋ እና ማንነት በአለም የማስተዋወቁን ስራ እየሰራ ይገኛል።

ከአርሶአደሩ ጓሮ ጀምሮ በአካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ለዓለም በማስተዋወቅ እና ዞኑ ከዚህ ማግኘት የሚገባውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዞኑ ተወካይ የሆኑት አቶ አዝመራ አንደሞ እንደተናገሩት የሸካ ዞን ለብዙ ዘመናት የሚዲያ ተደራሽነት ችግር የነበረበት አካባቢ እንደነበር እና ላለፉት 15 ዓመታት በዞኑ ሚዲያን ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ጥረት መደረጉን አንስተው አሁን ላይ በተጀመረው የለውጥ ጉዞ ውስጥ መሳካት ችሏል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የማሻ ኤፍ ኤም 103.8 እንዲከፈት ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን በማንሳት የሬዲዮ ጣቢያው ብዙ ኪሎሜትሮችን አልፎ በ103.8mhz በአዲስአበባ መደመጥ በመቻሉ እንደ አካባቢው ተወላጅና የዞኑ ተወካይ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የዞኑንና የክልሉን እምቅ ሀብት ሚዲያውን በመጠቀም ለአዲስአበባ ነዋሪዎች ለማሳወቅና ኢንቨስተሮችን የመሳብ አቅሙ ከፍተኛ ነው በማለት ለሀገርና ለአካባቢው ብልጽግና የሚሆኑ መረጃዎችንና ይዘቶችን ማድረስ ይገባልም ብለዋል።

አቶ ድለ ተስፋዬ በተመሳሳይ የሬዲዮ ጣቢያው በአዲስአበባ መደመጥ በመቻሉ መደሰታቸውን በመግለፅ በኤፍ ኤሙ የሚተላለፍ አስተማሪና አካባቢውን የሚያስተዋውቅ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

የማሻ ኤፍ ኤም 103.8 ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ታምሩ ጎዱ በበኩላቸው በሶስት መንገድ በተረስተሪያል፣በሳይተላይት እና በማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስን ዓላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑን በመናገር በአጭር ጊዜ ውስጥ በሳይተላይት ስርጭት ይጀምራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወረዳ መነሻ አድርጎ አዲስአበባ ላይ መደመጥ የቻለ ሚዲያ በመሆኑና የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በመያዝ የሚዲያ አድማሱን ማስፋት መቻሉን በመግለጽ አካባቢውን በሀገር እና በዓለም የማስተዋወቁ ስራ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

አክለውም ለዚህ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ላደረገው ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና ድጋፍ ላደረጉ ሁሉም አካላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ማንኛውም አዲስ አበባ የሚኖር ሰው በ103.8 ላይ የሬዲዮ ጣቢያውን ስርጭት መከታተል እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ አማኑኤል ምትኩ