November 23, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የተመድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት ውይይት አካሄዱ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ሥር የሚንቀሳቀሱ የዩኤን ኤጀንሲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ስትራቴጅክና ከፍተኛ አመራሮች ጋር በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ ÷ የዩኒቨርሲቲውን አቅም ለማሳደግ፣ የእውቀት ልውውጥን፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን እና የጋራ ተነሳሽነትን በመያዝ ከተመድ እና መሰል ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪና ረዳት ፀኃፊ ጀነራል ራሚዝ አልክባሮቭ÷ተመድ በተለያዩ ኤጀንሲዎችና ፕሮግራሞች በኩል እንደ የወንጀል ፍትህ እና የፀጥታ ዘርፍ ማሻሻያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ሙያዊ እና ቴክኒካዊ እውቀትን በማጋራት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመስራት ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በውይይቱ ዩኒቨርሲቲው ከሀገር አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ለፖሊስ መኮንኖች የትምህርት እድል በመስጠት በቀጠናው የሚስተዋሉ ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሕግ አስከባሪዎች፣ ሰብዓዊ መብቶች እና የወንጀል ፍትህ ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እና ማዕቀፎችን እንደሚያበረታታ መገለጹን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

FBC

You may have missed