January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ሩሲያ በዩክሬን በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ጦርነቱ እንዲቆም ትፈልጋለች ተባለ

ዩክሬን በበኩሏ ግዛቶቿን ከሩሲያ ሳታስመልስ ድርድር እንደማትጀምር አስታውቃለች.

ሩሲያ በዩክሬን በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል ድርድር ማድረግ እንደምትፈልግ ተገለጸ።

ሞስኮ ይህን የተኩስ አቁም ሃሳቧን ኬቭና ምዕራባውያን የማይቀበሉት ከሆነ ግን ውጊያውን እንደምትገፋበት ነው ለፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቅርበት ያላቸው ባለስልጣናት ለሬውተርስ የተናገሩት።

ፑቲን በቤላሩስ ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ የዩክሬኑን ጦርነት ለመቋጨትና ሰላም ለማስፈን ዳግም ድርድር መጀመር አለበት ብለዋል።

ድርድሩ “መሬት ላይ ባለው እውነታ” ላይ የተመሰረተ እንጂ በአንድ ወገን (ኬቭ) ፍላጎት ብቻ የሚመራ እንዳልሆነም አብራርተዋል።

ሞስኮ በአውደ ውጊያ የተቆጣጠረቻቸውን የዩክሬን ይዞታዎች ይዛ ተኩስ ለማቆም ያቀረበችው ሃሳብ በዩክሬን ውድቅ ተደርጓል።

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ኩሌባ “ፑቲን ጦርነቱን የማቆም ምንም አይነት ፍላጎት የለውም፤ የአለማቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ጥረት ብቻ ነው ከጦርነት ይልቅ ሰላምን እንዲመርጥ ሊያደርግ የሚያስችለው” ሲሉ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

አዲሱ የያዝነውን ይዘን ጦርነት እናቁም የሚለው የሞስኮ ምክረሃሳብ በቀጣይ ወር በስዊዘርላንድ ሊካሄድ በታሰበው የሰላም ጉባኤ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ያለመ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ግን ሞስኮ “ማለቂያ የሌለው ጦርነት” አትፈልግም ሲሉ ተደምጠዋል።

በዩክሬን ጦርነት መዋጋት ያልፈለጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን ሀገራቸውን ለቀው መውጣታቸው ይነገራል።

ይህም የፕሬዝዳንት ፑቲንን ተቀባይነት ዝቅ እንዳደረገው በቅርቡ የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች አመላክተዋል።

የጦርነቱ መቀጠልም ተጨማሪ ምልምል ወታደሮች ወደ ሩሲያ ጦር እንዲገቡ ስለሚያስገድድ የዩክሬንን 18 በመቶ ይዞታ የተቆጣጠሩት ፑቲን በያዝነው ቦታ ጦርነቱ ይቁም የሚል ሃሳብ እንዳላቸው ነው ሬውተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ያስነበበው።

ክሬሚያን ጨምሮ በሞስኮ የተያዙ ስፍራዎችን እናስመልሳለን ሲሉ የሚደመጡት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በ2022 ከፑቲን ጋር ምንም አይነት ድርድር ማድረግ የሚከለክል አዋጅ ማውጣታቸው ይታወሳል።

ፑቲን ዜለንስኪ ስልጣን ላይ እያሉ የሰላም ስምምነት ይፈረማል ብለው እንደማያምኑ የሚያነሱት የሩሲያ ባለስልጣናት፥ ሩሲያ ምናልባትም ከአሜሪካ ጋር ልትደራደር እንደምትችል አመላክተዋል።

Al-Ain