የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጃ ዱጉማ እና ሌሎች የጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የወባ በሽታ መርሃ ግብር ፒኤምአይ (PMI) ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።ውይይቱ በቀጣይ ዓመት የወባ ቁጥጥርና ማጥፋት ስራ ወቅት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራትን በጋራ ለይቶ ለመተግበር ያለመ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ዶ/ር መቅደስ፥ በኢትዮጵያ የወባ በሸታን በመቆጣጠር እና በበሽታው ምክንያት የሚከሰተውን ሞት በመቀነስ ረገድ የሚያበረታታ ውጤት ቢመዘገብም፤ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ የዝናብ መቆራረጥ፣ ድርቅና የሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ ባለፉት ዓመታት ለትንኝ መራቢያ ምቹ አጋጣሚዎች በመፈጠራቸው የወባ በሸታ ታማሚዎች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።ይህን ተከትሎም ሰው ሰራሸና ተፈጥሮዊ ተግዳሮቶችን ከግምት ያስገባ ፈጣን የወባ መመርመሪያ ኪት እና የወባ ትንኝ መከላከያ የመኝታ አጎበርን ያካተተ አዲስ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት።ሚኒስትሯ አያይዘውም፥ ፒኤምአይ የወባ መድሃኒትን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፥ መንግሥት የወባ ስርጭትን ለመግታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸው፤ በዚህ ረገድ ፒኤምአይ እያደረገው ስላለው ድጋፍ አመስግነዋል።መርሃ ግብሩ የወባ ስርጭትን ለመግታት በሚደረጉ ጥረቶች እንዲሁም በመረጃ አያያዝ ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
EBC
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።