July 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከጣልያን አቻቸው አድሚራል ጁሴፔ ካቮ ጋር ተወያዩ

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከጣልያን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አድሚራል ጁሴፔ ካቮ ድራገን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የኢትዮጵያ የመከላከያ ልዑክ በጣልያን ወገን በተደረገለት ግብዣ በሀገሪቱ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡

የልዑካን ቡድኑ ጣልያን ሮም ሲደርስም በከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

በዛሬው ዕለትም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከጣልያኑ አቻቸው አድሚራል ጁሴፔ ካቮ ድራገን ጋር በወታደራዊ ትብብሮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም÷ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሁለቱ ሀገራት መካከል እያደገ የመጣውን ግንኙነት አውስተዋል፡፡

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣልያን ያደረጉት ጉብኝትና ጠ/ሚ ጆርጂያ ሜሎኒ በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለሀገራቱ ግንኙነት መጠናከር አመላካች መሆኑን ጠቅሰዋል።

አድሚራል ጁሴፔ ካቮ ድራገን በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት በወታደራዊ ዘርፍ ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ገልጸዋል።

አድሚራል ጁሴፔ ካቮ ድራገን በበኩላቸው÷በሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ወታደራዊ ጉዳዮች ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

በዘርፉ በተለያዩ ደረጃዎች ያለውን ግንኙነት ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውንም በጣልያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

FBC