November 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በእርግዝና ወቅት ስለሚስተዋሉ ለውጦች ምን ያህል ያውቃሉ?

አንዲት ሴት ነፍሰ ጡር በምትሆንበት ጊዜ አካላዊ ፣ ሆርሞናል እና ስሜታዊ ለውጦችን ታስተናግዳለች፡፡

በእርግዝና ወቅት የአተነፋፈስ፣ የጡት፣ የዳሌ፣ የደም ኅዋስ መጠን እንዲሁም አጠቃላይ የሆነ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ ቆዳ ላይና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚስተዋሉ ለውጦች በአካላዊ ለውጥ ይካተታሉ፡፡

እንዲሁም ለእርግዝና አስፈላጊ የሆኑ ሆርሞኖች ከመደበኛው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ሲጨምሩ ሆርሞናል ለውጥ እንደሚባል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ሆርሞኖቹ በመጨመራቸው ምክንያት በመጠኑ የደም ግፊት መቀነስ ሲያሳይ በአንጻሩ የድካም ስሜት ሊኖር እንደሚችልም ነው የሚስረዱት፡፡

ስሜታዊ ለውጥ የሚባለው ደግሞ አንዲት ሴት በማርገዟ ምክንያት እንዲሁም በመውለድ ሂደት አዕምሮ ላይ በሚደርስ ጫናና ፍራቻ ሳቢያ የሚመጣ የባሕሪ ለውጥ ነው ይላሉ፡፡

በእርግዝና ወቅት ፊት ላይ ማዲያት፣ ሆድ ላይ ደግሞ እንደሸንተረር ቀለም ያላቸው ለውጦች የሚስተዋሉ ሲሆን÷ ክብደት መጨመር፣ እጅና እግር ላይ መጠነኛ እብጠት ወይም ያልተለመዱ ሁኔታዎች ሊታዩ እንደሚችሉም ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል በእርግዝና ወቅት በሚፈጠሩ የሆርሞን ለውጦች ምክንያት በሰውነት ውስጥ ያለው የደም መጠን ከፍ እንደሚል፤ የልብ ትርታም በአንድ ደቂቃ በአማካኝ በ15 ምት እንደሚጨምር እና የታችኛው የጉሮሮ ክፍል በቀላሉ እንደሚከፈት ይናገራሉ፡፡

እንዲሁም ጨጓራ ምግብ የመፍጨት ፍጥነቱ እንደሚቀንስ የሚናገሩት ባለሙያዎች÷ በዚህ ምክንያትም የማቃር እና ምግብ ያለመፈጨት ስሜት በበርካታ ነፍሰጡሮች ላይ እንደሚስተዋል ያነሳሉ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በተለይም በመጀመሪያዎቹ እርግዝና ወራት የማቅለሽለሽ እና የምግብ አለመስማማት ስሜት እንደሚኖር ያመላክታሉ፡፡

በዚህ ወቅት ከፍተኛ እና ተደጋጋሚ የሆነ ማስመለስ ከተስተዋለ እናት እና ጽንሱን ለአደጋ ብሎም ለሞት ሊዳርግ ስለሚችል የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መረጃ አመላክቷል፡፡

በነፍሰጡርነት ወቅት የሚስተዋሉ ለውጦች እርግዝናውን ተከትለው የመጡ መደበኛ ሁነቶች ናቸው ወይስ አደጋ የሚያስከትሉ ናቸው? የሚለው የሚለየውም አንዲት እናት ለመደበኛ ክትትል ወይም አጠራጣሪ ምልክቶች እንደታዩ ወደ ሕክምና በመሄድ ከሐኪሟ ጋር ስትመካከር መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

FBC