የኢትዮጵያን የገቢ መጠን ለማሳደግ ከተለምዷዊ አሰራር የተላቀቀና ዘመኑን የሚመጥን የገቢ አሰባሰብ ስርዓት መከተል ይገባል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ሀገራዊ የልማት፣ የሰላምና የፖለቲካ ክንውኖችን በጎርጎራ ገምግሟል።በመድረኩ በጉዳዮቹ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይም የገቢ ዘርፉ እያደገ መምጣቱን ካለፈው ዓመት ጋር በንፅፅር አቅርበዋል።በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከሁሉም የታክስ ዓይነቶችና ከቀረጥ 324 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን÷ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 374 ቢሊየን ብር መድረሱን ጠቅሰዋል።የጋራ ገቢ በ2015 ዘጠኝ ወራት 42 ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን÷ በተመሳሳይ ወራት ዘንድሮ 54 ቢሊየን ብር መድረሱንም ተናግረዋል።አጠቃላይ የሚሰበሰበው ገቢ ግን ከሀገሪቱ አቅምና ፍላጎት አኳያ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን እየተሰበሰበ ያለው ገቢ በእጥፍ ቢያድግ ለትውልድ የሚጠቅሙ በርካታ ፕሮጀክቶችን መገንባትና የሀገርን ብልፅግና እውን ማድረግ ይቻላል ብለዋል።የገቢ ዘርፍ ተቋማት ዘመኑን የሚመጥን የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በመከተል የግብር ስወራና ማጭበርበርን የመግታት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።የገቢ መጠንን ለማሳደግ ከተለምዷዊ አሰራር የተላቀቀና በቴክኖሎጂ የሚመራ ዘመኑን የሚመጥን የገቢ አሰባሰብ ስርአት መከተል ይገባል ብለዋል።የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ÷ በለውጡ ዓመታት በፈተናዎች ውስጥም ቢሆን የሀገር ውስጥ ገቢና ቀረጥ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ ቢመጣም ከኢትዮጵያ የመልማት አቅም እና ከሀገራዊ ምርት ያለው ድርሻ ሲታይ ውስን መሆኑ በግምገማው መነሳቱንም ጠቅሰዋል።በመሆኑም በቀጣይ በቴክኖሎጂ የታገዘ የታክስ አሰባሰብን ማጠናከርና የታክስ አስተዳደርን ማጥበቅ እንዲሁም የታክስ መሰረትን ማብዛትና የማስፋት ስራ ይከናወናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴና ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ዲጅታል አሰራር መዘርጋትና የድንበር አካባቢ ቁጥጥርን በማጥበቅ መስራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
FBC
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።