January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአፍሪካ ህብረት ገለጸ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር የሆኑትን አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬን ዛሬ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አምባሳደር ታዬ፥ የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር የተፈረመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነ በወቅቱ ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ባንኮሌ፥ የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት አበረታች መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሂደት ቁልፍ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚሁ ተግባር የአፍሪካ ህብረት ከሰላም ፈንድ ቋቱ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ማዕቀፍ የመጀመሪያዋ ተጠቃሚ አባል አገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ህብረቱ የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ማሰማራቱ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ቁርጠኝነቱን እንደሚያመላክት ተናግረዋል።

አክለውም፥ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ለማዳበርና ለማስፈጸም ስራም ህብረቱ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሁለቱ ወገኖች ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ወሳኝ በሆኑ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ባንኮሌ፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ማስፈን ጥረቶች ውስጥ ወሳኝና ውጤታማ አገር መሆኗን ተናግረው፤ ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚሻ ጠቁመዋል።

EBC