የእናቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር ከጀመረ 120 ዓመት ሊሞላው ጥቂት ዓመት ብቻ ቀርቶታል
የመንግስታቱ ድርጅት በየዓመቱ በፈረንጆች ግንቦት ወር ከገባ ሁለተኛው እሁድ የእናቶች ቀን ሆኖ እንዲውል በወሰነው መሰረት እለቱ ይከበራል።
እናቶች ለዓለማችን የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማስታወስ በሚል ከፈረንጆቹ ከ1907 ጀምሮ በየዓመቱ በመከበር ላይ ነው።
እናትነት በራሱ ጀግንነት ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈተናዎችን ተቋቁመው ለየት ያሉ ስራ የሰሩ እናቶች ደግሞ ይኖራሉ።
በዓለማችን በየቦታው ለልጆቻቸው እና ለዓለማችን እልፍ መልካም ስራዎችን ያበረከቱ እልፍ እናቶች ቢኖሩም በዚህ ዘገባችን ግን ጥቂቶቹን ብቻ እናነሳለን።
አበበች ጎበና ከ1928-2013 ዓ.ም
ዶክተር ካትሪን ሃምሊን 1924-2020
ኢትዮጵያዊቷ ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ለ41 ዓመታት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁም ነገር በማብቃት ከጀግና እናቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በ1972 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮ ድርቅ ሳቢያ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁለት ህፃናትን በመያዝ አበበች ጐበና ህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበርን መመስረታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።
አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ በመባል የሚታወቁት ክብርትዶ/ር አበበች በ41 ዓመታት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁነገር ያበቁ ሲሆን፤ በተለይዩ ድህነት ቅነሳ ፐሮግራሞች ከአንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሰጥተዋል።
አውስትራሊያቷ ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን ወደ ኢትዮያ መጥተው የፌስቱላ ሆስፒታልን ከኒውዚላንዳዊው ባለቤታቸው ዶክተር ሬጂናልድ ሐምሊን ጋር መስርተው ከ60 ዓመት በላይ አገልግለዋል።
በጽንስና ማህጸን ሙያቸው በፌስቱላ ችግር የሚሰቃዩ በርካታ ሴቶች ፈውስ አግኝተው ጤናማ ኑሮ እንዲገፉ አስችለዋል።
የማህጸን ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን በኢትዮጵያ ከ60 ሺህ በላይ በፌስቱላ የተጠቁ ሴቶችን ከስነልቦናዊ እና አካላዊ ቁስለት ለማዳን ችለዋል።
ሜሪ ኩሪ (1867-1934)
የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሜሪ ኩሪ በአደጋ ምክንያት ባሏን ብታጣም ሁለት ልጆቿን ከማሳደግ ጎን ለጎን በኬሚስትሪ ዘርፍ በሰራችው ምርምር የኖቤል ሽልማትን ማግኘት ችላለች።
ሳጁርነር ትሩዝ
የዓለማችን ጀግና እናት በመባል የምትታወቀው ሳጁርነር ትሩዝ ስትሆን በባርነት የተሸጠው የአምስት ዓመት ወንድ ልጇን ከባርነት ለማስለቀቅ ባደረገችው ተጋድሎ ጀግና ተብላለች።
ካቲ ሂድብ
የዓለማችን ጀግና እናት በመባል የምትታወቀው ካቲ ሂድብ ስትሆን ወላጅ አልባ ህጻናትን ለመርዳት ባደረጉት ጥረት ይታወሳሉ።
ይህች እናት በተለይም በዚምባብዌ፣ ህንድ፣ ቦስኒያ፣ ሜክሲኮ፣ ቦሊቪያ እና ዩጋንዳ ወላጅ የሌላቸውን ህጻናት በማሳደግ የዓለማችን ባለውለታ እንደሆኑ ተገልጿል።
ዋሪስ ድሬ
ሶማሊያዊቷ ዋሪስ ድሬ ሌላኛዋ የዓለማችን ጀግና እናት የተባለች ሲሆን በተለይም በ13 ዓመቷ የህጻንነት እድሜዋ የቀረበላትን ጋብቻ በመሸሽ ያሳለፈቻቸው ውጣ ውረዶች ከባድ ነበሩ ተብሏል።
ብዙ አስቸጋሪ የህይወት ምዕራፎችን በማለፍም ስኬታማ ሞዴል ለመሆን የበቃች ሲሆን በዓለም ላይ ያለእድሜ ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን የሚያስቀሩ ስራዎችን ማከናወኗ ተገልጿል።
ሳራህ ብሪድላቭ
የዓለማችን የመጀመሪያዋ በጥረቷ ሚሊየነር የሆነችው ጥቁር ሴት ሳራህ ብሪድላቭ ሌላኛዋ የምድራችን ጀግና እናት ተብላለች።
ይህች እናት የባሪያ ንግድ ሰለባ የነበረች ሲሆን የወደፊት ህይወቴ የባሰ አስቀያሚ ሳይሆን ከድህነት መውጣት አለብኝ፣ ለልጆቼም የተሻለ ሁኔታ መፍጠርም አለብኝ በሚል ወደ ንግድ ገብታ በጥረቷ እና በላቧ ስኬታማ በመባል የብዙ እናቶች አርዓያ መሆኗ ተገልጿል።
ኢሬና ሴንድለር
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከ2 ሺህ 500 በላይ አይሁዳዊያንን ከእልቂት የታደጉት ፖላንዳዊቷ ኢሬና ሴንድለር ደግሞ ተጨማሪ የዓለማችን ጀግና እናት ተብለዋል።
አይሁዳዊያንን ከናዚ እልቂት የታደጉት እኝህ እናት ድርጊታቸው መታወቁን ተከትሎ ብዙ መከራን የተቀበሉ እና እንዲገደሉ ቢፈረድባቸው በተዓምር ከሞት ተርፈው በፖላንድ መንግሥት የጀግና ሜዳሊያ ለመሸለም በቅተዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለማችን ብዙ ጀግና እናቶችን መጥቀስ ቢቻልም ለእርስዎ ጀግና እናት ማን ናት? ጀግና እናት ማለትስ ለእርስዎ ምን ማለት ነው? አስተያየትዎን ያካፍሉን።
Al-Ain
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።