July 2, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የነዳጅ እጥረት በሚፈጥሩ ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጀ

ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ÷ በኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ከማሸግ የዘለለ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሕጋዊ አሰራር አለመኖሩን ገልጸዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያም ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ማደያዎቹን ከማሸግ ያለፈ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

በአዋጁ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት በሚፈጥሩ ሕገ ወጦች ላይ እስራትና የገንዘብ ቅጣት እርምጃ መውሰድ የሚያስችሉ አንቀጾች መካተታቸውን ጠቁመዋል።

በአዋጁ ላይ ከነዳጅ ኩባንያዎች፣ከፈሳሽ ጭነት አሽከርካሪ ማህበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት መሰብሰብ መቻሉን ነው የገለጹት።

አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ተከትሎ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ባለስልጣኑ በዘርፉ ያለውን ሕገ-ወጥነት ለመከላከል ከአምስት ወር በፊት አዳዲስ የነዳጅ ማደያ ፈቃድ እንዳይሰጥ ክልከላ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ክልከላው የተደረገው ለነዳጅ ማደያ ግንባታ ራሱን የቻለ ደረጃና መስፈርት ባለመውጣቱ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን ለነዳጅ ማደያ ግንባታ የሚያስፈልግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጥራት መስፈርት ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

FBC