January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉን ርዕሳነ መሥተዳድሮች ተናገሩ

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር በቀል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉን የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መሥተዳድሮች ገለጹ፡፡ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማምረት እንዲሁም የግብርና እና ማዕድን ምርቶች ላይ ዕሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም የፋብሪካዎች ምርታማነት ማደጉን እና ትላልቅ የውጭ ኢንቨስተሮችም በማምረቻው ዘርፍ እንዲሰማሩ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡ክልሉ በግብርና ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን የፍራፍሬ፣ ቅመማቅመም፣ የማርና እንስሳት ተዋፅዖ ምርት እምቅ አቅም ስላለው የአካባቢው ማኅበራት ዕሴት የሚጨምር የምርት ማቀነባበር ሥራ ጀምረዋል ብለዋል፡፡የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በየክልሉ የሥራና የሀገር ምርትን የመጠቀም ባህል ላይ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በጨርቃጨርቅና ሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ 74 ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው በሙሉ አቅም ወደ ማምረት መግባታቸውንም አንስተዋል፡፡የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ÷ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ኢንቨስትመንት፣ የኢንዱስትሪና ከተማ ልማትን ጨምሮ በሌሎችም ሴክተሮች የሚታይ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተዘግተው የቆዩ 10 ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው÷ ይህም በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ በርካቶች እንዲሰማሩ ማስቻሉን ነው የተናገሩት፡፡የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የባለድርሻ አካላትን ጠንካራ የኢንዱስትሪ ልማት ቅንጅት የፈጠረና የዘርፉን ማነቆዎች የፈታ ነው፡፡ንቅናቄው በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ የጨውና ኬሚካል ኢንዱስትሪን ጨምሮ ከ100 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ አስችሏል ነው ያሉት፡፡የኃይል አቅርቦት፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታና የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሟላት በአንድ ማዕከል የባለድርሻ አካላት ትብብር ለችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

FBC