January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ጄት አበረረ

ኤአይ የጦር ጄት እንዲያበር መፍቀድ አንድ ቀን በሰዎች ላይ ቦምብ ሊጥል ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል

የአሜሪካ አየር ሀይል ኤአይ የጦር ጄት በረራ ሙከራ ከ20 ጊዜ በላይ አካሂዷል ተብሏል

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ጄት አበረረ።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲሺሻል ኢንተለጀንስ ተጽዕኖ እየጨመረ የመጣ ሲሆን አሁን ደግሞ የጦር ጄት አብራሪዎችን ለመተካት ሙከራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የአሜሪካ አየር ሀይል በኤአይ የታገዘ የጦር አውሮፕላን በረራ ሙከራ አድርጓል።

እስካሁን ቴክኖሎጂው ያለ ሰው እርዳታ በራሱ ለ20 ጊዜ የሙከራ በረራ ያደረገ ሲሆን ሙከራውን ተከትሎ በርካታ ባለሙያዎች ኮንነዋል።

ኤፒ የኤአይ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ኤአይ የጦር ጄቶችን እንዲያበር መፍቀድ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ብለዋል።

ቦምብ እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ለኤአይ መስጠት ሰዎች በተሰበሰቡበት ስፍራ ቦምብ በስህተት ሊጥል እና ሰዎች ሊጎዱ እንደሚችሉም ባለሙያዎቹ አስጠንቅቀዋል።

ሙከራውን ያደረገው የአሜሪካ አየር ሀይል በበኩሉ በኤአይ የታገዘ የጦር ጄት በረራ ሙከራው እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የበረራ ሙከራው በተለይም ለሰው ልጆች አደገኛ በሚባሉ አካባቢዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ፣ የጦር ጄት አብራሪዎችን ላለማጣት እና ፍጹም የሆኑ ጥቃቶችን ለማድረስም እንደሚጠቅም አስታውቋል።

በርካታ የዓለማችን ተቋማት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በስፋት እየተጠቀሙ ሲሆን ባለሙያዎች ግን ቴክኖሎጂው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ በማሳሰብ ላይ ናቸው።

ታዋቂው የዓለማችን ባለጸጋ ኢለን መስክ እና ሌሎችም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ኤአይ የሰው ልጆችን ቀስ በቀስ በመቆጣጠር ወደ አላስፈላጊ ፍጡራንነት ሊቀይር ይችላል ብለዋል።

AL-AIN