የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት በሠላም ተከብረዉ እንዲያልፉ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበሩት የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት በሠላም ተከብረዉ እንዲያልፉ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሻወኖ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሀይማኖታዊ በዓላቱ በሠላም እንዲከበሩ ዕቅድ ተዘጋጅቶ፣ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በበዓላት ሠሞን ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ጨምሮ እንደ ስርቆት፣ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ለገበያ ማቅረብ የመሳሰሉ ወንጀሎች እንደሚበራከቱ የተናገሩት ኮሚሽነር ሰብስቤ፣ መሠል ወንጀለኞችን ለመከላከል የክልሉ የፀጥታ አካላት ዝግጁ መሆናቸዉን ገልፀዉ፣ ህብረተሰቡ በግብይት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ አንዳለበት አሳስበዋል።
ከዚህ ባለፈ ከአደጋ የፀዳ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር አሽከርካሪዎች ትርፍ ከመጫን እና ከፍጥነት ወሰን በላይ ከማሽከርከር እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ ፣ በየአካባቢው ያሉ የትራፊክ ፖሊስ አባላት እና የመንገድ ደህንነት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ተገቢዉን ቁጥጥር እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የክልሉ ህዝብ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እና የአካባቢውን ሠላም በንቃት በመጠበቅ መሆን እንዳለበት ኮሚሽነር ሰብስቤ ሸዋኖ ገልፀዋል።
የህብረተሰቡን ሠላም እና ደህንነት ሊያዉኩ የሚችሉ ወንጀለኞችን እና ህገወጥ ተግባራትን ሲመለከት ህዝቡ በአቅራቢያው ላሉ የፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።