ትንሣኤ ተስፋ የሚያስቆርጡ በሚመስሉ ሁነቶች መሀል የተገኘ ብስራት ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የትንሳዔ በዓልን አስመልክተው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሐነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!
ትንሣኤ “መነሳት” ወይም “እንደገና መቆም” ነው፡፡ ትንሣኤ ከውርደት ወደ ክብር፣ ከመርገም ወደበረከት፣ ከማጣት ወደማግኘት፣ ከሞት እና ጉስቁልና ወደ አዲስ ሕይወትና ልዕልና በመሸጋገር በራስ ጸንቶ መቆምን የሚያስተምረን ነው፡፡
የትንሳኤ በዓል እየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ በዘር ከአዳም የወረሰውን እዳ ለመክፈል ሞትን አሸንፎ የተነሳበት፣ አስፈሪውን የጨለማ ሕይወት በትንሳኤ ብርሐን የለወጠበትና የተዘጋ የሚመስለውን የባርነት ሕይወት በአዲስ ተስፋና ነጻነት እንዲገለጥ ያደረገበት በዓል እንደሆነ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በጽኑ ይታመናል፡፡
ከትንሣኤ በፊት በትንሣኤው ባለቤት ዘንድ ሕማም ነበር፡፡ በአብዛኛዎቹ ተከታዮቹም ዘንድ መጠራጠር፣ ፍርሀት፣ ተስፋ መቁረጥና ክህደት ነበር፡፡ በጣም ጥቂቶች ግን የጥርጣሬው ወጀብ ሳይገፋቸው፣ የተስፋ መቁረጡ ማዕበል ሳይንጣቸው፣ የፍርሃት ቆፈን ሳይበግራቸው ተስፋ የሚያደርጉትን ትንሣኤ ለማየትና ዐይተውም ለማብሰር በጽናት ተጓዙ፡፡ በመጨረሻም በሀሳብ ያለሙትን በተግባር አዩ፡፡ የትንሣኤው ብርሃን ተሳታፊም ሆኑ፡፡ የማይሆን የሚመስለው ሁሉ በጊዜው ሆነ፡፡ ጨለማው በብርሃን ተተካ፤ በሀዘን የተዘራው ዘር ጎምርቶና አፍርቶ በደስታ ታጨደ፡፡ ሞቶ በስብሶ ይቀራል የተባለው ሙስና መቃብርን ድል ነስቶ ትንሣኤውን አበሰረ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደሀገር ለዘመናት እየተንከባለሉ በመጡ ዕዳዎቻችን ምክንያት ከዚህም ከዚያም በሚወረወሩ ሾተሎች ስትወጋ ቆይታለች፡፡ በውጭና በውስጥ የጥፋት ኃይሎች በተጋረጡባት ሳንካዎች እየተፈተነች ኖራለች፡፡ ሕመሟን የሚያክም፣ ሸክሟን የሚሸከም፣ ክብሯን የሚመልስና ዝናዋን የሚያድስ ትውልድ በማስፈለጉ በብዙ መስዋእትነት ለውጡ እንዲወለድ ሆኗል፡፡
ለውጡን ተከትሎም የጨለመና የተጋረደ የሚመስለው በብርሐን እየደመቀ፣ ውሉ የጠፋበት ቋጠሮና ትብታብ እየተፍታታ፣ ገደልና ሸለቆው እየተደላደለ፣ ማዕበሉና ውሽንፍሩ እየሰከነ መሄዱን ሁላችንም እያረጋገጥነው የሚገኝ እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ያሉትን ሁሉንም ፈተናዎቿን ተቋቁማ በአሸናፊነትና በክብር እንደምትሻገር ከትንሣኤው ልንማር ይገባል፡፡ በተግባርም ትናንት ያስጎነበሱን ጽኑ ሸክሞቻችን ዛሬ ቀስ በቀስ እየተራገፉ ቀና ብለን መራመድ ጀምረናል፡፡
በምጥ የተወለደው ለውጥ አድጎና ጎርምሶ የኢትዮጵያን ትንሣኤ እንዲያበስር ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለሀገራችን ሕመም የሆኑትን ተነጣይ ትርክት፣ ባንዳነት፣ የተደራጀ ሌብነት፣
አሉባልታና ስንፍናን በመጸየፍ እና በጽናት በመታገል አዲስ የሥራና የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ የአገራችን ትንሳኤ በፅኑ መሰረት ላይ እንድናስቀምጥ የጀመርነውን ሁለንተናዊ ርብርብ አጠናክረን እንድናስቀጥል በዚህ አጋጣሚ አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
በድጋሚ መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ!
አገኘሁ ተሻገር
የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ
ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም.
FBC
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።