November 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በኢትዮጵያ የነባርና የዲጂታል ሚዲያዎች መበራከት የፕሬስ ነፃነት መብት ተጠቃሚነት እያደገ ለመምጣቱ ተጨባጭ ማሳያ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በኢትዮጵያ የነባርና የዲጂታል ሚዲያዎች መበራከት የፕሬስ ነፃነት መሰረታዊ መብት ተጠቃሚነት በአገሪቱ እያደገ ለመምጣቱ ተጨባጭ ማሳያ ነው ሲል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። 

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የሚገኙ አንዳንድ ኤምባሲዎች የሰጡትን የጋራ መግለጫ መመልከቱን የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር ፅኑ አቋም አለው ብሏል። 

ይህ መብት ሊተገበር እና ሊጠበቅ የሚገባው ደግሞ በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው። 

በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የነባር እና የዲጂታል ሚዲያዎች ቁጥር መብዛትም የዚህ መሰረታዊ መብት ተጠቃሚነት በአገሪቱ እያደገ ለመምጣቱ ተጨባጭ ማሳያ እንደሆነም መግለጫው ጠቅሷል። 

ኢትዮጵያ ከአጋሮቿ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኩል ገንቢ ግንኙነትን ትቀበላለች ብሏል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው። 

ሆኖም በተደጋጋሚ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ በመሰባሰብ በደቦ የሚወጡ መግለጫዎች ለሁለትዮሽ ግንኙነት የማይጠቅሙ እንዲሁም ከተለመደውና ቅቡልነት ካለው በሁለትዮሽ የዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ከተመሠረተው ግንኙነት ደንቦችና አሰራሮች ጋር የሚጣረሱ መሆኑን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ገልጿል።

EBC