November 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ትውልዱ በሀገረ መንግስት ግንባታ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ

ትውልዱ በሀገረ መንግስት ግንባታው ላይ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) አመላከቱ፡፡

“የምሁራንና ወጣቶች ሚና ለሀገረ መንግስት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ዋና ጽ/ቤት በተዘጋጀው 2ኛ ዙር የፓናል ውይይት፤ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ፈቲ መሃዲ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።

እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ወጣት ምሁራንም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።

ትውልዱ ከሀገር ተረካቢነት ባለፈ በሀገረ መንግስት ግንባታው ላይ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ያመላከቱት አይሻ (ኢ/ር)፤ ወጣቱ በልማቱ ያለውን ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዚህም ሀገርን በሚጠቅሙ እና በሚያሳድጉ እንደ ሜጋ ፕሮጀክቶች እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ዶክተር ፈቲ በበኩላቸው ወጣቱ እንደ ሀገር ኢትዮጵያን ለመገንባት አስተዋጽኦ ሊያደርግ በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ በአፍሪካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆንና አፍሪካን ለመምራት በማሰብ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በውይይት እና በሃሳብ ልዕልና የሚያምን ትውልድ መገንባት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

FBC