November 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የሀሳብ ልዩነቶችንና የትጥቅ ግጭቶችን በምክክር ከመፍታት ሌላ አማራጭ የለም – ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የሀሳብ ልዩነቶችንና የትጥቅ ግጭቶችን በምክክር ከመፍታት ሌላ አማራጭ የለም – ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የሀሳብ ልዩነቶችን እና የትጥቅ ግጭቶችን በምክክር ከመፍታት ሌላ አማራጭ እንደሌለ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቷ ይህን የተናገሩት በቀጣይ በክልል እና በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው የምክክር ጉባኤ የሴቶች ተሳትፎ ሚናን የተመለከተ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ያሉ ችግሮችን ከስረ መሰረቱ ለመፍታት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጀምሮ የሚደረጉ ንግግሮችና ድርድሮች ሴቶችን እያሳተፉ ባለመሆኑ ይህ ሊስተካከል ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ምክክሩን አካታች ማድረግ ከተቻለ ኢትዮጵያውያን የሚተማመኑበት ውይይት ማድረግ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የ120 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እጣ ፋንታ የሚወሰንበት እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፤ የተሳካ እንዲሆን ቀናነት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

የንግግር ልምድ መገንባት አለመቻሉ የችግሮች ሁሉ ምንጭ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፤ ሰላምን ለማረጋገጥ መነጋገር ወቅቱ የሚጠይቀው አጀንዳ ነው ብለዋል።

የህዝቦችን ፍላጎት በትክክል በመረዳትና የተሳካ ምክክር በማድረግ ደም አፋሳሽ የሆኑ ግጭቶችን ማስቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ከውይይትና ከንግግር በኋላ የሚስተዋለው የአፈፃፀም የትግበራ ችግር እንዳይኖር ሊታሰብበት እንደሚገባም ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል።

EBC