July 2, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ወጣቱ ስራ ፈጣሪ መሆን እንዳለበት ተገለፀ ።

ወጣቱ ትውልድ ስራ ጠባቂ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ መሆን እንዳለበት ተገለፀ ።የስራና ክህሎት ሚንስቴር ከኢንተርፕርነር ሺፕ ዲቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ( EDI) ጋር በመተባበር ለቴፒ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች እና መምህራን በሥራ ፈጠራ ላይ የሚያተኩር ስልጠና ሰጥቷል።በተቋሙ አሰልጣኝና የቢዝነስ አማካሪ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ሽብሩ ተቋሙ ከ9 አመት በላይ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለወጣቶች፣ለሴቶችና በተለያዩ ስራ ላይ ለተሰማሩ አካላት በስራ ፈጠራና ተያያዥ ዘርፎች ስልጠናዎችን በመስጠት ሠልጣኞች ከራሳቸው አልፎ ለሀገር እንዲበቁ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።እስከ አሁን ከ140 ሺህ በላይ ወጣቶችን ማሰልጠን መቻላቸውንም ተናግረዋል ።አሁን ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውስጥ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ስልጠናዎችን በመስጠት ተመራቂ ተማሪዎች ስራ ጠባቂ ከመሆን ወጥተው ስራ እንዲፈጥሩ እየሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል ።የስልጠናው ዋና አላማ ወጣቱ ትውልድ ከስራ ጠባቂነት በመውጣት ስራ በመፍጠር ከራሱ አልፎ ለሀገር እንዲተርፍ ለማስቻል ነው ብለዋል።EDI የተባለው ፕሮጀክት ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቀጣይ 5 አመታት ውስጥ ከ1ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ይህን ስልጠና ለመስጠት አቅዶ በመስራት ላይ እንደሆነም አቶ ስንታየሁ ገልፀዋል ።ከቴፒ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ከ1 መቶ በላይ ተመራቂ ተማሪዎችን እያሰለጠኑ መሆናቸውን ገልፀው እነዚህ ተማሪዎች በተማሩት ሙያ ስራ ሳይጠብቁ ስራ ፈጥረው እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ነው ብለዋል።ለእነዚህ ወጣቶች ምቹ የስራ ሁኔታ ከመፍጠር ጀምሮ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የሚመለከተው አካል መስራት እንዳለበት ገልፀው ለዚህም ከከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል ።አሁን ላይ የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መብዛት የአለም አቀፍ አጀንዳ እንደሆነ ገልፀው ከዚህ ችግር ለመውጣት እንደ ሀገር ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።ከሰልጣኞች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት እየተሰጠ ያለው ስልጠና በተማሩት የስራ ዘርፍ ማንግሥትን ሳይጠብቁ ስራ ፈጣሪ በመሆን ከእራሳቸው አልፎ ለሀገር እንዲበቁ የሚያስችል ነው ብለዋላ።ተመርቀው በሚወጡበት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ፣ስራ እንዴት መፍጠር እንዳለባቸው እንዲሁም ከእራሳቸው አልፎ ለሀገር እንዴት መብቃት እንዳለባቸው የተሰጠው ስልጠና ከፍተኛ እንደነበረም ሰልጣኞች ተናግረዋል።

ዘጋቢ ትእግስት በዛብህ