January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን የትምህርት ቤቱን አቅም ለማጎልበት እየተሰራ ነው::

በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን የትምህርት ቤቱን አቅም ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ የይና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገለፀ።

የወረዳው ትምህርት ፅህፈት ቤት በበኩሉ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ትርፍ መሬቶች ላይ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብሏል።

የይና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ተስፋለም ደጊቶ እንደገለፁት ትምህርት ቤቱ የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንና በዚህም የስንዴ፣ድንችና ጥቅል ጉመን የማልማት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በራስ ተነሳሽነት ገቢን በማሳደግ ለመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችን የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ሀላፊው በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በበጀት አመቱ ከመንግስት የሚደረግ የድጎማ በጀት ያለመኖሩን የገለፁት አቶ ተስፋለም የውስጥ ገቢን በማሳደግ የተጓደሉ መጻሕፍትን፣ ጀኔሬተርና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግባቶችን በመግዛት የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዲጠናከር መደረጉንም ጠቁመዋል።

የማሻ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ወንድወሰን እስራኤል በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ለትምህርት ቤቶች ሲሰጥ የነበረዉ የድጎማ በጀት መቆሙን ተከትሎ ጠባቂነትን ለማስቀረት በወረዳው የሚገኙ 27 ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸዉን ተናግረዋል።

ከስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ውጭ መሬት ፆም ማደር የለበትም በሚል ወደ ስራ በመገባቱ ድንች፣ጥቅል ጎመንና የበጋ ስንዴን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉን የገለጹት ሀላፊዉ የወረዳው ፋይናንስ እንዲሰበሰብ ያወጀው የውስጥ ገቢ እስከ 7መቶ ሺህ ብር ቢሆንም እስከ የካቲት 30 ድረስ 6መቶ 84ሺህ 4መቶ 72 ብር በውስጥ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ :- በዛብህ ታደሰ